በክ/ከተማዉ ወረዳ 3 በተዘጋጀው የስንቅ ዝግጅት መረሃ ግብር ላይ የከተማና የክ/ከተማ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዉ ስንቅ የሚያዘጋጁ ነዋሪዎችን አበረታተዋል።
የክ/ከተማው ዋና ስራ አሰፈጻሚ ዶ/ር አበራ ብሩ የስንቅ ዝግጅቱ ላይ ተገኝተው ነዋሪዎችን ባበረታቱበት ወቅት እንደተናገሩት የሀገር መከታና አለኝታ የሆነውን መከላከያን ለመደገፍ በክፍለ ከተማው በርካታ ስራዎች የሚሰሩ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ በሚደረጉ ድጋፎች ህብረተሰቡ ከመከላከያ ሰራዊታችን ጎን በመቆም አስዋጽዖ ማበርከት ይገባል ብለዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈጻሚው አያይዘውም በቀጣይ ደም በመለገስ እና የስንቅ ዝግጅት በማድረግ ደጀንነታችሁን የበለጠ ማጠናከር አለባችሁ ሲሉ ተናግረዋል።
መከላከያ ሰራዊቱን በመወከል በስንቅ ዝግጅቱ የተገኙት ልፍተናንት ኮሎኔል ትዕግስት ፈረደ ለ3ኛ ጊዜ በተከፈተብንን ወረራ ለመቀልበስ በምታደርጉት የደጀንነት ድጋፍ ላይ በመገኘተ በመከላከያ ስም ኩራትና ክብር ተሰምቶኛል ብለዋል።
የወረዳ 3 አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ደንኤል ሰይፉ ለሀገሩ ክብር እየተዋደቀ ለሚገኘው መከላከያ ሰራዊትና ጥምር ጦሩ ስንቅ ዝግጅት ላይ መሳተፍ የሚያስመሰግን በመሆኑ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
በስንቅ ዝግጅቱ ላይ የተሳተፉት ነዋሪዎች የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ሀገራችንን ለሚጠብቀው መከላከያ ሀይላችን ተከፍሎ የማያልቅ ውለታ አለብን በማለት በሁሉም ግንባር ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
ነዋሪዎቹ ለሀገር መከላከያ ሰራዊትና ጥምር ጦሩ ደጀን ከመሆን ባሻገር አገባቢያችን በመደራጀት ከሰርጎ ገቦችና ከጸጉረ ልውጦች ነቅተን እየጠበቅን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የስንቅ ዝግጅቱ በክ/ከተማዉ በሁሉም ወረዳዎች እየተከናወነ ይገኛል።