የአብርሆት ቤተመጽሀፍት መንግስት ለህዝቡ የገባዉን ቃል በተግባር መፈጸሙን ያረጋገጠበት መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
ከ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ በአዲስ አበባ አራት ኪሎ አካባቢ የተገነባው አብርሆት ቤተ-መፃህፍት ምረቃት ላይ ከንቲባ አዳነች እንደተናገሩት፥ አዲስ አበባን እንደስሟ ውብ እናደርጋታለን ብሎ መንግስት ቃል በገባው መሰረት በርካታ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት እንደበቁ አስታውሰዋል፡፡
አገሪቱ በተለያዩ ግንባሮች ብዙ ጦርነት የተከፈተባት ቢሆንም፥ መስዋዕት በመክፈል ውስጥ ህይወትን፤ በግንባር እየወደቁ ቀና ማለትን፤ በፈተናዎች ውስጥ ማሸነፍን ፤ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር ሀገሪቱ ማየቷን አንስተዋል ፡፡
በመስዋትነት ወድቀው ዛሬ ቀና እንድንል ያደረጉ እና ኢትዮጵያን ከመፍረስ ላዳኑ የመከላከያ ሰራዊት እና የጸጥታ አካላት ዘላለማዊ ክብር ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
በጦርነት ውስጥ ብንሆንም የልማት ስራዎቻችንን ከመስራት አልተቆጠብንም ያሉት ከንቲባዋ፥ ይልቁንም በእልህ እና በቁጭት በሁሉም ዘርፎች በመስራት ኢትዮጵያዊ አይበገሬነታችንን አሳይተንበታል ፤ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ያሸነፈችው ኢትዮጵያ መሆኗንም ተናግረዋል።
የትምህርት ተቋማት የዜጎች መብቀያዎች ፣ለነገ አገር ተረካቢዎች መገኛዎች መሆናቸውን የጠቆሙት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፥ አውቀትን አላምጦ ለመዋጥ ደግሞ የቤተ መጽሃፍቶች ሚና የጎላ መሆኑን አስምረውበታል።
ዛሬ የተመረቀው አብርሆት ቤተመፃህፍት በግዝፈቱ እና በዘመናዊነቱ በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚው መሆኑን አመልክተዋል።