የጥገና ስራው ከሁለት ወር በፊት የጀመረው
የአትላስ ድልድይ አሁን ላይ አጠቃላይ አፈፃፀሙ ከ65 በመቶ በላይ ደርሷል፡፡
ከአትላስ ወደ ኡራኤል ቤተ ክርስቲያን በሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኘው ይህ ድልድይ 35 ሜትር ርዝመትና 10 ሜትር ከፍታ ያለው ነው፡፡
ድልድዩ ለረጅም ጊዜ ያገለገለ ከመሆኑም ባሻገር ወደ ወንዙ በሚጣል ከፍተኛ መጠን ያለው ደረቅ ቆሻሻ በመሞላቱ የተነሳ በክረምት ወራት የሚፈጠረው ከፍተኛ የጎርፍ ውሀ የድልድዩን ተሸካሚ የመሰረት ግንብ እንዲቦረቦር በማድረጉ የድልድዩ ድጋፍ ግንብ የመሰንጠቅና የመናድ አደጋ አጋጥሞትም ነበር፡፡
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትና መልሶ ጥገና ለማድረግ እንዲያስችለው ከድልድዩ ስር የተከማቸውን ከፍተኛ መጠን ያለው ቆሻሻ በማንሳት የቅድመ ዝግጅት ስራ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
አሁን ላይ የተጎዳውን የድልድዩን መሰረት ለማጠናከር እስከ 3 ሜትር ጥልቀት በመቆፈር የኮንክሪት ሙሌትና የተቦረቦረውን የድልድዩን ተሸካሚ ድጋፍ ግንብ መልሶ የመጠገን ስራ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ቀሪ ስራዎችንም በቀጣይ አጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡
የጥገና ስራው እስከሚጠናቀቅ ድረስ ከአትላስ ወደ ኡራኤል የሚሄዱ አሽከርካሪዎች ወደ ድልድዩ ጠርዝ ባለመጠጋት ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ እንዲያሽከረክሩ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እያሳሰበ የአካባቢው ማህበረሰብም የጥገና ስራው ከተጠናቀቀ በኋላ ድልድዩ ስር ቆሻሻ ባለመድፋት የጋራ የሆነውን የመንገድ ሀብት በጋራ እንዲጠብቅ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡