የአንዳንድ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያን የመምራት ድብቅ አጀንዳቸውን ገሀድ ያወጣ ተግባር ልንገታ ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት የአንዳንድ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያን የመጠምዘዣ እጅ ነው የምንለው በምክንያት ነው ብለዋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት ተኩስ ማቆምን የሽንፈት ምልክት አድርጎ ሲወስድ፣ በኢትዮጵያ ሰራዊትና ህዝብ ወኔ ላይ ሲሳለቅ፣ በእብሪት ተሞልቶ ንፁሀንን በመጨፍጨፍ ወደ አጎራባች የአማራና የአፋር አካባቢዎች ለመስፋፋት በርካታ ጥቃቶችን ሲሰነዝር፣ ህፃናትና ሴቶችን በጅምላ ሲጨፈጭፍ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ዝምታን የመረጡ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት በዚህ ሰዓት ከየአቅጣጫው የተኩስ አቁም ጥሪ ላይ መሆናቸውን ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ የተኩስ አቁም ጥሪው የከሀዲ ድርጅቱን ህይወት በማራዘም በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያን የመምራት ድብቅ አጀንዳቸውን ገሀድ ያወጣ ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል ።
በመሆኑም መላው ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የዚህን የእናት ጡት ነካሽ ቡድን አረመኔያዊ ድርጊት ለማጋለጥና አንዳንድ አገራትና ዓለምአቀፍ ተቋማት የያዙትን የተሳሳተ ግንዛቤ በፍጥነት እንዲያርሙ ለማድረግ እስካሁን ከሰራነው በላይ ተጠናክረን ልንታገል ይገባል ብለዋል፡፡