በውይይቱ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ኪነጥበብ ሀገርን በመገንባት ፣ዜጋን ለመቅጽ ፣ ሰላም እና አንድነትን በማጠናከር እና ህዝብን ለልማት በማነሳሳት ትልቁ መሣሪያ ነው ብለዋል ።የከተማዋን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ የልማት ስራዎች እንዲያሳኩ ፣የታየው የሰላም እና ሀገራዊ አንድነት ይበልጥ እንዲጠናከር የኪነጥበብ ባለሙያዎች በሙያቸው እያበረከቱት ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል ።የኪነጥበብ ባለሙያዎች ሀገራዊ ለውጡ እንዲመጣ የተጫወቱት ሚና የላቀ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባዋ ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረው በሙያቸው የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል ።የኪነጥበብ ባለሙያዎች በተለይ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በህግ ማስከበር ዘመቻ ፣በታላቁ ህዳሴ ግድብ እና ሌሎች ድጋፎች እንዲደረጉ ህበረተሰቡን በማነሳሳት ያደረጉት ተሳትፎ አጅግ የላቀ መሆኑን ገልጸዋል ።
በከተማዋ እየተገነቡ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የኪነጥበብ ዘርፉን ማዕከል ያደረጉት መሆናቸውን የገለፁት ወ/ሮ አዳነች የአድዋ ዜሮ ኪሎሜትር ሙዚየም እና ሌሎች ፕሮጀክቶች የባህል እና የኪነጥበብ ማንጸባረቂያ ናቸው ብለዋል ።አጠቃላይ የኪነጥበብ ዘርፉ እንዲጠናከር በእቅድ እና በፓሊሲ እንዲደገፍ የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ወ/ሮ አዳነች ተናግረዋል ።ከውይይቱ በኃላም የአዲስ አበባ ከተማ ባህል ፣ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ከኢትዮጵያ የኪነጥበብ ማህበራት ጋር በትብብር ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል ።