የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ከኢትዮጲያ ንግድ ባንክ ጋር የተፈራረመው የመግባቢያ ስምምነት የከተማ አስተዳደሩ የከተማውን ነዋሪ የቤት ችግር ለመቅረፍ ካቀረባቸው አማራጮች አንዱ የሆነውን በ2005 የ20/80 እና የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ልማት ፕሮግራም ተጠቃሚ ለመሆን የተመዘገቡ እንዲሁም ፍላጎት እና አቅሙ ያላቸውን ነዋሪዎችን በህብረት ስራ ማህበር በማደራጀት ቤት እንዲያለሙ የሚያደርገውን አማራጭ ወደ ትግበራ ምዕራፍ ለማስገባት የብድር አገልግሎት ለማመቻቸት ያለመ ነው፡፡
ከተማ አስተዳደሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በህብረት ስራ ማህበር ለማልማት የሚያስፈልገውን አሰራር ስርዓት ለመዘርጋት በተዘጋጀው መመሪያ እንደተመላከተው ፍላጎት ኖሮኣቸው የተመዘገቡ ነዋሪዎች የግንባታ ወጪውን 70% ያህል ቆጥበው 30% ደግሞ ቢሮው ከፋይናንስ ተቋማት የብድር አቅርቦት እንደሚያመቻች በተገለፀው መሰረት በአሁኑ ወቅት በቤት ልማት ዘርፉ በፋይናንስ አቅርቦት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ ካለው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር አገልግሎቱን ማግኘት ተችሏል።
ቢሮው ባደረገው ጥሪ መሰረት ፍላጎት አሳይተው ከተመዘገቡት 12,000 በላይ ቆጣቢዎች ውስጥ 4,580 የሚሆኑት በዳግም ምዝገባው ተገቢውን መረጃ ይዘው የቀረቡ በመሆኑ በመጀመሪያው ምዕራፍ ወደ ትግበራ የሚገቡ ናቸው፡፡
በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የተዘገቡት 4,580 በላይ ቆጣቢዎች በ57 ህብረት ስራ ማህበራት እንዲደራጁ የመደልደል ስራ ተጠናቋል፡፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ፍላጎትን መሰረት አድርጎ ከአንድ ማህበር ወደ ሌላ ማህበር ለመቀያየር በሚቀመጥ ቀነ ገደብ ውስጥ ተከናውኖ ሲጠናቀቅ በአ/አ የህብረት ስራ ማህበር ኤጀንሲ ተደራጅተው ህጋዊ ሰውነት እንዲያገኙ የማድረግ ስራ የሚሰራ ይሆናል፡፡ በቀጣይ ተገቢውን ቅድመ-ሁኔታ አሟልተው ህጋዊ ሰውነት አግኝተው በህብረት ስራ ማህበር ሲደራጁ የፕሮጀክት ሳይት እና የብሎክ እጣ በማውጣት የመሬት ርክክብ ለማህበራቱ በማድረግ ግንባታ የሚጀምሩ ይሆናል።
ከዚህ በተጨማሪ በርካት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን እነዚህም የአሰራር ስርዓት መዘርጋት፤ በከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊው የመሬት አቅርቦት ዝግጅት፤ የህንፃ ዲዛይን ስራ፤ ከአአ የህብረት ስራ ማህበር ኤጀንሲ በቀጣይ ስራ ስምምነት እንዲሁም የዛሬውን ከባንክ ጋር የፋይናንስ ብድር አቅርቦት ማመቻቸትን ያካትታል፡፡