የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመወያየት ያዘጋጀው የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ እና የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አለማየሁ እጅጉ የአዲስ አበባ ከተማ ያላትን ምቹ ሁኔታ የሚረዳ እና ያሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን የሚፈታ ተቋም በማስፈለጉ አካዳሚው መቋቋሙን ገልፀዋል።
አቶ አለማየሁ የተዘጋጀው የውይይት መድረክ የዜጎችን የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ ለመፍታት የሚያስችሉ እና የአገልግሎት አሠጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚረዱ ሀሳቦች የሚነሱበት ይሆናል ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የአካዳሚው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ደሳለኝ ጴጥሮስ በበኩላቸው አመራሩንና ፈፃሚ ባለሙያውን በምርምርና ጥናት ላይ የተመሠረተ ሳይንሳዊ ሥልጠና እንሰጣለን ብለዋል።
በሚሰጠው ሥልጠና የመፈፀምና የማስፈፀም አቅምን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ ጠቁመው፤ ለሥልጠናው መሳለጥ እንዲህ አይነት መድረኮች ወሳኝ መሆናቸውን አስታውቀዋል።