በውይይት መድረኩ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ዘርፈሽዋል ንጉሴ እንዳስታወቁት ምክር ቤቱ ባለፉት 8 አመታት በህዝብ የተሰጠውን ተልዕኮ እና አደራ ለማሳካት ባደረገው ጥረት በርካታ ስኬቶችን በማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
የአስፈጻሚው አካል ህብረተሰቡን በልማት እና በተለያዩ ዘርፎች ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሰራቸውን ስራዎች አሰፈላጊውን ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ በተለይ የመንገድ፤ ውሃ፤ እና ሌሎችም የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እንዲሻሻል በየደረጃው የሚገኙ የምክር ቤት አባላት የበኩላቸውን ጥረት ማድረጋቸውን አፈጉባኤዋ ተናግረዋል፡፡
ምክር ቤቱ በስኬት ካከናወናቸው ስራዎች መካከል የከተማዋን ሁለንተናዊ እድገት ወደፊት ማስቀጠል የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ደንቦችን እና አዋጆችን ከማጽደቅ ባለፈ ህብረተሰቡ በልማቱ እንዲሳተፍ እስከ ወረዳ ድረስ ባሉ የምክርቤቱ መዋቅር ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡
ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰብ ስራ ፣የመከላከያ ስራዊት ድጋፍ ፣የአቅመደካማ ነዋሪዎች የቤት እድሳት እና የማዕድ ማጋራት እና በሌሎች ተግባራት በባለፉት አመታት አበረታች ውጤት ማስመዝገብ እንደተቻለ ወ/ሮ ዘርፈሽዋል ገልጸዋል፡፡
የፊታችን መስከረም ላይ ለሚመሰረተው አዲሱ ምክር ቤትም መስመር የሚያሳይ ስራ ሰርቷል ያሉት አፈጉባኤዋ የቀጣዩ ምክር ቤት ተግባርም በአንድ በኩል ልማትን በማፋጠን የሚጥርበት በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚጥረውን አካል የምንከላከልበት መሆን አለበትም ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት፣የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ የክፍለ ከተማ እና ወረዳ አፈጉባኤዎች በውይይቱ ተሳትፈዋል፡፡