ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩን የ2013 ዓ.ም የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለምክር ቤቱ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ ።በኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አዳራሽ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወ/ሮ ዘርፈሽዋል ንጉሴ ጉባኤውን የከፈቱ ሲሆን በበጀት ዓመቱ 6 ወራት በከተማዋ በማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊ እና ሌሎች ዘርፎች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል ።በተለይ የተጀመሩ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች አጠናቆ ለህዝብ አገልግልት እንዲውሉ መደረጉ፣ ለረጅም አመታት ሲንከባለሉ የመጡ ህገወጥ የመሬት ወረራ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የተወሰደው ህግን የማስከበር እርምጃ ፣ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ፣የታላቁ ህዳሴ ግድብ ድጋፍ ፣የተማሪዎች ምገባ፣ የላፍቶ እና ሌሎች የገበያ ማዕከላት እና የአበበች ጎበና የእናቶች እና ህጻናት ሆስፒታል ተጠናቀው ለአገልግሎት መዋል፣ የአዳዲስ ሆስፒታሎች እና ሌሎችም ፕሮጀክቶች እንዲጀመሩ የተደረገው ስራ ለአብነት አንስተዋል ።በቀሪ ስድስት ወራትም የተጀመሩት ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥል እና 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በትኩረት መሰራት እንዳለበት አፈጉባኤዋ ገልጸዋል።