በአዲስ አበባ ከተማ ትልቅ የስፖርት ማዕከል ለመገንባት ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑንና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ እና የስፖርት ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ወ/ሮ አዳነች አበቤ ገልጸዋል።
13ኛ የአዲስ አበባ ከተማ ስፖርት ምክር ቤት መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ እና የስፖርት ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ወ/ሮ አዳነች አበቤ በተገኙበት የተካሄደው ጉባዔ በከተማዋ ስፖርት እድገት ላይ ተግዳሮት ናቸው የተባሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል።
ከምክር ቤት አባላቱ ለተነሱት ጥያቄዎች ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ ምላሽ እና ማብራሪያ ስጥተዋል።
ከንቲባዋ የስፖርት ማህበረሰቡ መስተጋብሩን እንዲያጠናክር በማድረግ ለከተማው ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ በመሆኑ ለዘርፉ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የከተማው ስፖርት በሚፈለገው ልክ ላለማደጉ እንደምክንያት የሚነሳው እና ባለፋት አመታት በተደጋጋሚ ተጠይቆ መፍትሄ ያልተገኝለት ደረጃውን የጠበቀ የስፖርት ማዕከል ግንባታ ጉዳይም በጉባኤው ምላሽ አግኝቷል ።
የከተማው የስፖርት ምክር ቤት ሰብሳቢ ወ/ሮ አዳነች አበቤ ለግንባታው የሚሆን ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የስፖርት ማዕከል ግንባታው በቀጣይ በጀት አመት እንደሚጀመርም ከንቲባዋ አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል በከተማዋ የሚስተዋለውን የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ችግር ለመቅረፍ 60 የስፖርት ማዘውተሪያ በታዎች መጠናቀቃቸውን የተናገሩት ከንቲባዋ የከተማውን ፕላን በጠበቀ መልኩ ቦታዎቹን የማዘጋጀት ስራ ቀጣይነት ይኖረዋል ብለዋል።
ከንቲባዋ በቀጣይ ለሁሉም የስፖርት አይነቶች ትኩረት በመስጠት እንደሚሰራ የተናገሩ ሲሆን በዋናነት ሰፖርት የኢትዮጵያን ገፅታ የመቀየር ትልቅ ሀይል ያለው በመሆኑ በአለም አቀፍ መድረክ ሀገራቸውን መወከል የሚችሉ ስፖርተኞችን ማፍራት ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
*