ከንቲባ አዳነች አቤቤ የባህል ማዕከል መገንቢያ ቦታውን ለጎፋ ዞን አመራሮች በዛሬው ዕለት አስረክበዋል ።
በመርሐግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፣የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚንስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ፣የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ጌትነት በጋሻው፣የፌዴራል ፣የአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ አመራሮች እና የዞኑ ተወላጆች ተገኝተዋል ።
የጎፋና ኦይዳ ባህል ማዕከል በአዲስ አበባ ከተማ መቋቋም ከተማዋ የሁሉንም ኢትዮጽያዊያን ብሔር ብሔረሰቦች የባህል ሙዚየም እንድትሆን ማሳያ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመርሐግብሩ ገልጸዋል ።
በተጨማሪም የከተማዋን የቱሪዝም ዘርፍ በማሳደግ ገቢ ከማመንጨት ባለፈ የህዝቦችን አንድነት እና ፍቅር ከማጠናከር አንጻር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል ።
የባህል ማዕከሉ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የዞኑ ተወላጆች ተባብረው መስራት ይኖርባቸዋል ፤የከተማ አስተዳደሩም አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የጎፋ ዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ጌትነት በበኩላቸው ከወራት በፊት ለከተማ አስተዳደሩ የጎፋና ኦይዳ ህዝብ ባህልን ለማስተዋወቅ በቀረበው ጥያቄ መሠረት ፈጣን ምላሽ በመሰጠቱ ምስጋና አቅርበዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ጎፋ ሰፈር በሚል ስሜ በሚታወቀው ስፍራ የጎፋ ዕድገትና ብልፅግና ልማት ማህበር በይፋ ተመስርቷል ።
በእለቱም ለከንቲባ አዳነች አቤቤ ከጎፋ ዞን በስጦታ የተበረከተላቸውን ሰንጋ በሬ አሸባሪው ህውሃት በከፈተው ጦርነት በወሎ አካባቢ ለተፈናቀሉ ዜጎች እንዲሆን አበርክተዋል ።