የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የ500 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።
ህብረተሰቡን በማስተባበርም በገንዘብ እና በቁሳቁስ ለመደገፍ እስከ 2 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተገልጿል ።
“ክብር ለሀገራችን አንድነት እና አብሮነት ለቆሙ ለጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን “በሚል የአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ ጉዳዮች ፣ለሰራዊቱ በሚደረግ የድጋፍ እና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ዙሪያ ወይይት ተካሂዷል ።
በውይይቱ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደገለፁት
የመከላከያ ሰራዊት በትግራይ ክልል የነበረውን ችግር በመቅረፍ ፣በህግ ማስከበር እና የኢትዮያን ሉዓላዊነት ከማስከበር አንጻር ትልቅ ገድል ፈጽሟል ብለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩም ለመከላከያ ሰራዊቱ ደጀን በመሆን ካሁን በፊትም እንዳደረገው አሁንም በማንኛውም ሁኔታ ሰራዊቱን ለመደገፍ የ500 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል ።
በተጨማሪም ህብረተሰቡን በማስተባበር ሰራዊቱን በገንዘብ እና በቁሳቁስ ለማጠናከር የከተማ አስተዳደሩ እስከ 2 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ጠቁመዋል ።
የፌዴራል መንግስት የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ክልል የተናጠል የቶክስ አቁም ማወጁ ትክክለኛ እና ተገቢ መሆኑን ገልፀው ህብረተሰቡ በጁንታው የውሸት ፕሮፓጋንዳ ሳይደናገር በከተማዋ የተጀመረውን የልማት ፣የሰላም እና ሌሎች ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ የብልጽግና ተስፋ የሆነውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት ለማጠናቀቅ ህብረተሰቡ አካባቢውን በንቃት መጠበቅ እንዳለበት ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል ።