ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የባህል መገንቢያ ቦታውን ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን አስረክበዋል ።
የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጠባቂ፣ የበርካታ ባህላዊ ትውፊቶች መገኛ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የሕውኃት የሽብር ቡድን ይህ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር መኖር እንዳይችል ሲያናቁረው ኖሯል ብለዋል ።
የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በተሻለ ሁኔታ ባሕሉን ማሳደግ ይቻለው ዘንድ የባሕል ማዕከል መገንቢያ ስፍራ መዘጋጀቱን ምክትል ከንቲባዋ አመልክተዋል ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ቋንቋዎችና ባሕሎች ባለቤት ናት ፤ ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን ባህሎቻችንን በመጠበቅ ለሀገራችን ዕድገት እና ዘላቂ ጥቅም በሚያስገኝ መልኩ መንከባከብና ማሳደግ እንደሚገባ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል ።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው የአዲስ አበባ እና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ግንኙነት የረጅም ጊዜ መሆኑን ጠቅሰው በቅርቡም በአሶሳ ከተማ ስም የተሰየመ ትምህርት ቤት ለአብነት አንስተዋል።
የመላው ኢትዮጵያ ከተማ ፤የአፍሪካ እና የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መኖሪያ በሆነችው አዲስ አበባ የክልሉን ባህል ለማስተዋወቅ የከተማ አስተዳደሩ ላደረገው የቦታ ስጦታ በክልሉ መንግስት እና ህዝብ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
የክልሉ መንግስት እና ህዝብም በጋራ ሆነው የባህል ማዕከሉን በፍጥነት ለማጠናቀቅ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አቶ አሻድሊ ሀሰን ገልጸዋል ።
የባህል እና ቱሪዝም ሚንስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳ በበኩላቸው የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ሀብቶች የበለጸገ መሆኑን ገልፀው የክልሉን ባህል የሚያንጸባርቅ የባህል ማዕከል በአዲስ አበባ መገንባት ለቱሪዝሙ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል ።
ማምሻውን በተካሄደው የርክክብ መርሐግብር የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሽናፊ፣ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የከተማ አስተዳደሩ እና የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል ።