የአዲስ አበባ አስተዳደር ካቢኔ ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ በ2014 በጀት ዓመት ለካፒታል እና መደበኛ ስራዎች፤ የከተማዋን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠል እና የነዋሪዎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ለማስቻል በአጠቃላይ 70 ቢሊዮን 670 ሚሊዮን 216 ሺህ 028.31 ብር በጀት በመወሰን ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት መርቷል፡፡
የ2014 በጀት ድልድል በ2013 በጀት ዓመት ከተያዘው በጀት ጋር ሲነጻጸር በ9 ቢሊዮን 319 ሚሊዮን 594 ሺህ613.31 ብር ወይም የ15.19% ዕድገት አለው ተብሏል፡፡
ከተማ አስተዳዳሩ የቀጣይ 10 ዓመት እና 5 ዓመት መሪ ዕቅድን የተመለከቱ የትኩረት አቅጣጫዎችንና ስትራቴጂክ ግቦችን መሰረት ባደረገ መልኩ በ2014 በጀት ዓመት ለኮንስትራክሽን ዘርፍ፤ ለውሃና ፍሳሽ ዘርፍ፤ ለመንገድ ልማት ዘርፍ፤ ለትምህርትና ስልጠና ዘርፍ፤ ለትራንስፖርት ዘርፍ፤ የአረንጓዴ ልማት ዘርፍ፤ ጤና ዘርፍ እና ለቤቶች ልማት ዘርፎች ከፍተኛ በጀት ተመድቦላቸዋል፡፡
በከተማ ደረጃ ለሚገኙ የማዕከል መስሪያ ቤቶች በጠቅላላው 46 ቢሊዮን 559 ሚሊዮን 320 ሺህ 315.98 ብር የተመደበ ሲሆን ከአጠቃላይ በጀት ውስጥ 65.88% ድርሻ አለው፡፡
ለማዕከል መ/ቤቶች ከተመደበው በጀት ውስጥ ለመደበኛ ብር 16 ቢሊዮን 248 ሚሊዮን 362 ሺህ 343.73 (22.99 %) እና ለካፒታል ብር 30 ቢሊዮን 310 ሚሊዮን 957 ሺህ 972.25 (42.89%) ተደልድሏል።
ለክፍለ ከተሞች የተመደበ በጀት ደግሞ 24 ቢሊዮን 110 ሚሊዮን 895 ሺህ 712.33 ብር ከአጠቃላይ በጀት (34.12 %) ድርሻ አለው፡፡ ከዚህ ውስጥ ለመደበኛ በጀት ብር 20 ቢሊዮን, 541 ሚሊዮን 879 ሺህ 040.39 ብር (29.07 %) እና ለካፒታል ደግሞ 3 ቢሊዮን 569 ሚሊዮን 016 ሺህ 671.94 ብር (5.05 %) በመሆን ተደልድሏል።
በጀቱን ታክስ ከሆኑና ካልሆኑ፤ ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች፤ ከሌሎች ምንጮች ማለትም ከብድርና ከዕርዳታ እንዲሁም ካለፈው በጀት ዓመታት ተራፊ ካሽ በጀቱን ለሟሟላት በእቅድ መያዙን ታውቋል፡፡