የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በድርቅ ምክንያት ለተጎዱ ወደ 2.4 ሚሊዮን የሚገመቱ ወገኖች የሚሆን የአንድ መቶ ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው የምግብ ቁሳቁስ እና የእለት ደራሽ ድጋፍ በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አማካኝነት ለክልሉ ፕሬዘዳንት አቶ ሙስጠፌ ኡመር አስረክበዋል፡፡
በድጋፍ ማስረከቡ ወቅት አስተያየታቸውን የሰጡት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት ህመማችሁ ህመማችን ነው ፤ችግራችሁ ችግራችን ነው፤ እናንተ ላይ የደረሰው ጉዳት ሁላችንም ላይ የደረሰ ነው ይሰማናል! በማለት ገልፀዋል፡፡
ይህንን በስሜት ብቻ ሳይሆን በአካል መጥተን አብሮነታችንንና አብረናችሁ መሆናችንን ማሳየት ይኖርብናልም ብለዋል፡፡
እንደ ከንቲባዋ አገላለፅ ሃገራችን አሁን የገጠሟትን ችግሮች መሻገር የቻለችው አብረን በመቆማችን ነው ያሉ ሲሆን አሁንም አብረን ከሆንን አሁን የገጠመን ችግር እጅግ ቀላል ነው፤ እናልፍዋለን፤ ይህንን የማድረግ ጉልበትም አቅምም እሴትም ልምድም አለን በማለት ተናግረዋል፡፡
ድጋፉም ይህ የመጀመርያ ዙር ነው ያሉት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በዚህኛው ዙር ለምግብ ቁሳቁሶች ቅድሚያ የሰጠነው ቅድሚያ ለሰው መስጠት ስለሚያስፈልግም ነው ብለዋል፡፡
የሶማሌ ክልል ፕሬዘዳንት አቶ ሙስጠፌ ኡመር በበኩላቸው፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሶማሌ ክልል የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም ሃገራዊ ግዴታውን ለመወጣት የበኩሉን እያደረገ ነው ያሉ ሲሆን እኛም ጥያቄውን ስናቀርብ ከተማ አስተዳደሩ ለሰጠን ፈጣን ማላሽ ማመስገን እፈልጋለሁ በማለት ገልፀዋል፡፡
በክልሉም ድርቁ ወደ ርሃብ እንዳይቀየር ሰፊ ርብርብ እየተካሄደ መሆኑንና መንግስት የአጭርና የረጅም ጊዜ ስራዎችን አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡