የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለመኖ የሚሆን የእንስሳት ሳር እና የተለያዩ የምግብ ቁሳቁሶችነ በዛሬው ዕለት አስረክበዋል ።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንደገለጹት ምንም እንኳን ሀገራችን በተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥ ብትሆንም በኢትዮጵያዊ አንድነት እና አብሮነት ጀግናው የመከላከያ ሰራዊትን እና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎችን በሞራል እና በተለያዩ ተግባራት ለማገዝ ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ ድጋፍ ስናግዝ እና ስናበረታታ ቆይተናል፣በቀጣይም አጠናክረን እንቀጥላልን ብለዋል፡፡
አሁንም በቦረና ዞን በድርቅ ምክኒያት የተጎዱ ዜጎችን ለመደገፍ እንዲሁም በወሎ እና አካባቢው ህውሃት በከፈተው እኩይ ጦርነት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ እና ጉዳት እንዳይደርስባቸው የከተማ አስተዳደሩ ነዋሪዎችን እና ባለሀብቶችን በማስተባበር ድጋፉን መሰባሰቡን ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡
ለወገኖቻችን ደራሾች እኛው ነን ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሌሎች አካላት በተለያዩ መንገድ እርዳታ ሊሰጡን ይችላል ነገር ግን እረዳታው ይዞብን የሚመጣው ጣጣ እያየን በመሆኑ ኢትዮጵያዊን ከተጋገዝን እና ከተረዳዳን አቅማችንን ማሳየት እንችላለን ብለዋል፡፡
የቦረና ነዋሪዎች ከሶሰት ወራት በፊት ከብት እና ፍየሎችን በመያዝ ሲረዱ ቀይተዋል፤ አሁን ግን በተከሰተው የተፈጥሮ ድርቅም ሳቢያ ጉዳት ላይ በመሆናቸው የከተማ አስተዳደሩ በቀጣይም አሰፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ከንቲባዋ ጠቁመዋል፡፡
የቦረና ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጃርሶ ቦሩ በበኩላቸው አዲስ አበባ የኢትዮጵያዊያን ዋና ከተማ ብቻ ሳትሆን የሁሉም እናት ናት፤ልጅ ሲቸገር ደግሞ ወደ እናቱ ነውና የሚጮህው የከተማ አስተዳደሩ እና የከተማዋ ነዋሪዎች ላደረጉት ድጋፍ በቦረና ዞን ስም አመስግነዋል።
የከተማ አስተዳደሩም ዛሬ ባደረገው ድጋፍ መሰረት ለቦረና ዞን በድርቅ ለተጎዱት 16 የውሃ ቦቴ ፣11 ተሳቢ መኪና የእንስሳት ሳር እና ሁለት መኪያ የተለያዩ የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡
በተጨማሪም ለወሎ እና አካባቢው ለተፈናቀሉ 7 ሚሊየን ብር የሚገመት አምስት ተሳቢ መኪና የምግብ ፣የአልባሳት እና የንጽህና መጠቢቂያ ድጋፍ አድርጓል፡፡