በሃገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በደረሱ የድርቅ አደጋዎችና በጦርነት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማውን ህብረተሰብ በማስተባበር የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
በዛሬው እለትም በባሌና ምስራው ባሌ ዞን በተፈጥሮ አየር መዛባት ምክንያት ለድርቅ አደጋ የተጋለጡ ወገኖቻችንን ለመርዳት የከተማው አስተዳደር ከባለሃብቶችና ከከተማው ማህበረሰብ ያሰባሰበውን ከ78 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የእለት ደራሽ ድጋፍ አበርክቷል፡፡
ድጋፉን ያበረከቱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት
በመካከላችሁ የተገኘነው አይዟችሁ ወገን አላችሁ፤ የእናንተ ችግር የኛ ችግር ነው ለማለት ሲሆን ይህንንም በመናገር ብቻ ሳይሆን በተግባር ችግራችሁን በመካፈል አብረናችሁ እንዳለን ልናሳይ ነው ብለዋል፡፡
ባሌ የሚታወቀው በጀግንነትና ያለውን በማካፈል ነው ያሉት ክብርት ከንቲባዋ የባሌ ህዝብ ሰው ውሃ ጠማኝ ካለ ወተት ቀድቶ ነው የሚያጠጣ ህዝብ ነው ብለዋል፡፡
አሁንም ይህ ችግር በገጠመው ወቅት ከዚህ ህዝብ ጎን መቆም ለኛ ኩራት ነው ብለዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች ከ78 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት እርዳታ ከህዝብ መሰብሰቡን አውስተው ፡ ከጎደሎው ያካፈለንን የከተማው ነዋሪዎች እናመሰግናለን ብለዋል፡፡
ወደፊትም የከተማ አስተዳደሩና የአዲስ አበባ ህዝብ በማንኛም ጊዜ ከባሌ ህዝብ ጎን እንደሚቆም ገልፀዋል፡፡
አቶ አብዱላኪም አሊዪ የባሌ ዞን ዋና አስተዳደር በድጋፍ ርክክብ ወቅት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤና የከተማው አስተዳደር እንዲሁም መላው የከተማው ህዝብ እኛ እያለን የባሌን ህዝብ ድርቅ አያጠቃዉም ፤ እኛ እያለን የባሌ ህዝብ አይራብም በማለት በርካታ ሃገራዊ ጫና እያለባቸዉ ከባሌ ህዝብ ጎን ለመቆም ዛሬ እኛ ጋር በመገኘታቸዉ ከልብ እናመሰግናለን ብለዋል፡፡
አቶ እሸቱ በቀለ የምስራቅ ባሌ ዋና አስተዳደርም በበኩላቸው የከተማው ህዝብ በሁሉም ቦታዎች ለኢትዮጵያዊ ወገኖቹ እያረገ ያለውን አስተዋፅኦ በባሌ ህዝብ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡