የከተማ አስተዳደሩ በመላው ሃገራችን እያጋጠሙ ባሉ የተለያዩ የተፈጥሮም ይሁን በጦርነት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ፈጥኖ በመድረስ ሰብአዊ ድጋፎችን እርዳታዎችን መላውን ህዝብ በማስተባበር ለወገኖቹ አለሁላችሁ ሲል መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ዛሬም በጉጂ ዞን በድርቅ ምክንያት ለጉዳት የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍል በተለይም በድርቁ ምክንያት የሚላስ የሚቀመስ አጥተው እየሞቱ ላሉት ለከብቶችና እንስሳት የሚሆን የሳርና የመኖ እንዲሁም የውሃ ማጠራቀሚያ ሮቶ ድጋፎችን ለዞኑ አስተዳደርና አባገዳዎች ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አስረክበዋል፡፡
ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት ‹‹የዛሬው ድጋፍ ዋና አላማ አብረናቸው እንደሆንን ለማሳየትና ፍቅራችንን ለመግለፅ ነው፡፡›› ብለዋል
‹‹ጉጂ አንድንም በድርቅ ሁለትም ደግሞ በፀጥታ ችግር እየተሰቃየ ነው›› ያሉት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች ‹‹አካባቢው ወደ ተረጋጋ ሁኔታ እስኪመለስ ድረስ አንለያችሁም ፤ድጋፋችም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡››
‹‹አካባቢው ሰላም ሲሆን ደግሞ መጥተን እንጎበኛችኋለን፤ ትልቅ የሆነውን ፍቅራችንንም እናንተ ጋር ማድረስ ይቻለናል›› በማለት ገልፀዋል፡፡
የጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ኦዶ በበኩላቸው በዞኑ ባጋጠመው ችግር ምክንያት ህብረተሰቡ ከብቶቹ ግመሎቹና ፍየሎቹ እያለቁበት መሆኑን ገልፀው ማህበረሰቡ አሁን አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡
ላቀረብነውም ሃገራዊ ጥሪ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እጅግ ፈጣን ምለሽ ስለሰጠንም እናመሰግናለንም ብለዋል፡፡
የጉጂ አባገዳዎችም ለከተማ አስተዳደሩ ድጋፉን ላስተባበሩ አካላት በህዝቡ ስም ስጦታ አበርክተዋል፡፡