የከተማ አስተዳደሩ የከተማውን የፀጥታ ችግሮች ለመቅረፍ ሲያሰራቸው የቆያቸውና ከ320 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያደረገባቸው ሶስት የተለያዩ ዘመናዊ የፖሊስ መምርያ ህንፃዎችና ከ511 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸውን ከ100 በላይ ፕሮጀክቶች በዛሬው እለት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ም/ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ ፤ በም/ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ ፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ሌሎች የከተማው የካቢኔ አባላት እንዲሁም የተለያዩ እንግዶችና የፓሊስ ሰራዊቱ አመራሮችና አባላት በተገኙበት አስመርቀዋል፡፡
በምርቃቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች እንደተናገሩት ኢትዮጵያን የማደናቀፍ እቅድ የያዙ ሃይሎች ብዙ እኩይ ተግባር በሚያካሂዱበት በዚህ ሰዓት ቃላችንን ጠብቀን ፤በርካታ ፕሮጀክቶችን መርቀን ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ በመቻላችን እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ ብለዋል፡፡
ከተማችን አዲስ አበባ የሀገራችን ዋና ከተማ ፣ዓለም አቀፍ ሦስተኛ የዲፕሎማሲ ማዕከልና የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ እንደመሆኗ የፖሊሳዊ አገልግሎት ተደራሽነትን ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ በማሳደግ ለልማታችን በሚሆን መልኩ የከተማችንን ሁለንተናዊ ሰላም ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል
በዚህ አጋጣሚ ለአዲስ አበባ ፖሊሶች መልእክት ያስተላለፉት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች ፡ራሳችሁን ለህዝብ ሰጥታችሁ የእውነትና የቃል ኪዳን ቃላችሁን ጠብቃችሁ በሰብአዊነት ማገልገል በሚለው መርህ ህዝብ ማገልገላችሁን እንድትቀጥሉ ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ክፍያችሁም ሌላ ነገር አይደለም፤ በእርግጥ ቃል የገባችሁለት ሙያችሁ ተከብሮ ማየት ነው ብለዋል፡፡ ይህ ሞራል ይሆናችኋል ፤ይህ ለስራችሁ ስንቅ ይሆናችኋል ሲሉም ገልፀዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስን ለማጠናከር ማንኛውንም አይነት ድጋፍ በማድረግ በኩል የሚሰስተው ነገር እንደሌለም ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች ገልፀዋል፡፡
እንዲሁም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጌቱ አርጋው በበኩላቸው ባለፉት ጊዜያት የከተማው ፖሊስ ከህብረተሰቡ ጋር ባደረገው ብርቱ ጥረት ወንጀልን በመቀነስ በኩል አበረታች ለውጥ መታየቱን ገልፀዋል፡፡
በተለይም የፀረ ሰላም ሃይሎችን ሴራ በማክሸፍ በከተማዋ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን ተችሏልም ብለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩም ፖሊስን ለማጠናከር እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው አሁንም የከተማ አስተዳደሩ በሁሉም ክ/ከተሞች ተመሳሳይ የፖሊስ ተቋማትን እንደሚያስገነባ ገልፀዋል፡፡
አቶ ጀማል ረዲ የኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አስተዳደሩ እስከ ግመሽ ለሊት ድረስ ተሰልፎ የመረጠውን ህዝብ ቃል የገባለትን ለመፈፀም በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝና ዛሬ የዚህ አካል መሆኑን አውስተዋል፡፡
የፖሊስ መምርያ ህንፃዎቹ ውጪ ዛሬ የተመረቁት የኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ፕሮጀክቶች ለወጣቶችና ለሴቶች የስራ እድል የሚፈጥሩ ሼዶች ፤ ለረጅም ጊዜ የህዝብ ጥቄ የነበሩ 11 የጤና ተቋማት ፤ ትምህርት ቤት ማስፋፍያ ግንባታዎችና ለተማሪዎች የመመገብያ አገልግሎት የሚሰጡ የመመገቢያ አዳራሾች ፤ የስፖርት ማዘውተርያ ቦታዎች ፤ የህፃናት መዋያ ቦታዎች ፤ የህዝብ መፀዳጃዎች ይገኙበታል፡፡