ድጋፉን ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ፤በምክትል ከንቲባ ማእረግ የማዘጋጃ ቤታዊ ዘርፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ ጋር በመሆን በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በጉዲና ቱምሳ የስልጠና ማዕከል በመገኘት አስረክበዋል ።
ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት ሰሞኑን በጣለው ከባድ ዝናብ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ መካነየሱስ ሴሚናር ቤተክርስቲያን ጊቢ እና ሌሎች አካባቢዎች በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ቤተሰቦች እና ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችን ለማገዝ ይገባል ብለዋል ።
በቀጣይም የከተማ አስተዳደሩ ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለሟቋቋም እና መሠል የጎርፍ አደጋዎች ዳግም እንዳያጋጥሙ አስፈላጊው ስራ እንደሚከናወን ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰለሞን ፍሰሃ በከተማዋ የጎርፍ አደጋ በተከሰተባቸው በአጉስታ፣ ወይራ፣ መካኒሳ እና ጎፋ አካባቢዎች ለሚገኙ 650 ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የዛሬውን ሳይጨምር ከ1ሚሊዮን 532ሺህ ብር በላይ የአይነት እና የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ገልፀዋል ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተጎጂ ቤተሰቦች የሚውል ከ1 ሚሊየን 389 ሺህ ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከ216 ሺህ ብር በላይ ወጪ የተገዙ የተለያዩ ቁሳቁስ እንዲሁም የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የ100 ሺህ ብር በጠቅላላው ከ1.7 ሚሊዮን በር የሚገመት የገንዘብ እና የአይነት ድጋፍ ለተጎጂዎች ተበርክቷል።
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ፕሬዝዳንት ቄስ ዮናስ ይገዙ በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ የጎርፍ አደጋው ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ለተጎጂዎች የህክምናና ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ ያሳየው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል ።