የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲሱ ካቢኔ አንደኛ አመት የመጀመሪያ ሰብሰባውን በማካሄድ የተለያዩ ውሳኔዎች አስተላለፈ።
በዚሁ መሠረት:-
1.የአዲስ አበባ የመዋቅራዊ ጥናት ማሻሻያ ላይ በዋናነት መሠረታዊ የህዝብ ጥያቄዎች ለሚነሳባቸዉ ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት እና በተለይም በመንገድ ግንባታ፣ በአረንጓዴ ልማት ፣በህንጻ ከፍታ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እና በአጠቃላይ በከተማዋ የፕላን ትግበራዎች ላይ የታዩ ክፍተቶችን ለማረም በሚያስችሉ የመፍትሄ ሀሳቦች ዙሪያ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።
2.በህብረተሰቡ ላይ የሚደርሰውን የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናን ለማቃለል ለተለያዩ ተቋማት የበጀት ድጎማ እንዲደረግ ካቢኔው ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን የከተማ አስተዳደሩ ለሸገር ዳቦ ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍሎች ወቅታዊውን የገበያ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ 309ሚሊዮን 337ሺህ 500 ብር ድጎማ እንዲዉል የወሰነ ሲሆን በተመሳሳይም የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እህት ኩባንያ የሆነዉ ሆራይዘን ፕላንቴሽን የ199 ሚሊዮን 837ሺህ 500 ብር ድጎማ የሚያደርግ ይሆኗል ።
በተጨማሪም የተማሪዎች ምገባ የዋጋ ማሻሻያ ሰነድ ላይ ውይይት በማድረግ ለ2014 የትምህርት ዘመን 1.9 ቢሊዮን ብር ድጋፍ እንዲደረግ ወስኗል ።
በተያያዘም የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የመዋጮ መጠን እንዲወሰን እና በከተማዋ ከ231ሺህ በላይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ዉስጥ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የጤና መድህን ሽፋን አገልግሎት ለመስጠት የ 144 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በአስተዳደሩ እንዲደረግ ወስኗል።
የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ቡድንን የፋይናንስ አቅም ለማጠናከር የሚያስችል የ70 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንዲደረግለት ካቢኔ ከውሳኔ ላይ የደረሰ ሲሆን የስፖርት ቡድኑ በዘላቂነት ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረዉና በፋይናንስ የራሱን የገቢ ምንጭ መፍጠር የሚያስችለዉ የተለያዩ አማራጮችን እንዲፈጥር ከዉሳኔ ላይ ደርሷል።
በመጨረሻም በሀገሪቱ ለተለያዩ አካባቢዎች ለማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማገዝ እና ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ጊዜአዊ ኮሚቴ እንዲዋቀር አቅጣጫ በማስቀመጥ መደበኛ ስብሰባው ተጠናቋል ።