የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ ጋር በመተባበር መሬትና መሬት ነክ ጉዳዮች እና የፍርድ ቤት ግዜያዊ እግዶች በሚል ሃሳብ ባዘጋጁት ረቂቅ ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ብርሀነመስቀል ዋጋሪ፣ ዳኞች ፣አቃቢያን ሕጎች ፣የፍትህ ቢሮ ባለሙያዎችን ጨምሮ መሬትና መሬት ነክ አገልግሎት በቀጥታ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ረቂቅ የጥናቱ ግኝትና የመፍትሔ ሃሳብ ቀርቦ ጥናቱን ለማዳበር የሚያስችል ውይይት ተደርጎበታል
ኬዞችን ብቻ እያነሳን በየግዜው ክርክር ከምናደርግ የመሬት አያያዝን በዘላቂነት ለማሻሻል የሚረዱ ጥናቶችን በማድረግ መፍትሔ ማበጀት ብንችል ጠቃሚ ይሆናል ያሉት ከንቲባዋ በጥናቱና በውይይቱ ላይ እንደግኝትና መፍትሔ የሚነሱ ሃሳቦችን ተቀብለን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ ነን ሲሉ አስታወቀዋል
በጥናቱ ላይ እንደተመላከተው ሆን ተብሎ የሁላችንም ውስን ሀብት የሆነውን መሬት በፍርድ ቤት በእግድ ምክንያት ግለሰቦች እንዲበለጽጉበና ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍልን የሚጋፉ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ያሉበት ወቅት በመሆኑ ጥሰቱን በአጭር ፣በመካከለኛና በረጅም ግዜ እንደየጥሰቱ እንደግዝፈቱ ለይተን በጋራ እርምጃ በመውሰድ የሕግ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባራችን ይሆናል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል ።
460 የሚሆኑ የተለያዩ የሕግ ጥሰቶች የፈጸሙ የመሬት ጉዳይ ባለሙያዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዳችን የሚታወስ ነው ያሉት ከንቲባዋ አሁንም ተጠያቂነትን በሕግ ብቻ እያረጋገጥን ዘላቂ መፍትሔ ማስፈን የሁላችንም ባለድርሻ አካላት ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫ ይሆን ዘንድ ይገባል ሲሉ አስምረውበታል ።
በቀጣይም ቋሚ መድረክ እየተዘጋጀ ውይይቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያሳሰቡት ከንቲባ አዳነች
ሁላችንም ጋር እውነተኛ የሆነ ተጠያቂነት ሊሰፍን ይገባል ያሉት ከንቲባ አዳነች የፈለገ ወርቅ ህግ ብናወጣ አላማውን እንዳይስት አሰራርን ልናበጅ ይገባል ብለዋል
ለሁላችንም እድል የሰጠው ህዝብ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች ህዝቡን ትተን ብቻችንን ለዚህ መፍትሄ ልናመጣ አንችልም፤ህዝቡን ልናሳትፈው ይገባል፤ የራሱንም አስተዋፅኦ የሚያበረክትበትም አሰራር ሊኖር ይገባል በማለት ገልፀዋል፡፡
በውይይቱ በከተማችን እየተገነቡ ያሉ የመንገድ ፕሮጀክቶች ፣ከተማ አስተዳሩ በበጀት ዓመቱ ልሰራቸው የነበሩ ልዩ ልዩ ፕሮጀክት ፣የተገጣጣሚ ቤቶች ልማትና መሠል ሕዝብን ማዕከል ያደረጉ የልማት ሥራዎች በፍርድ ቤት ግዜያዊ ዕግድ ምክንያት መስተጓጐላቸው በጥናቱ ላይ የተመላከተ ሲሆን አፋጣኝ መፍትሄ ልሰጣቸው ይገባል ተብሏል።
ፍርድ ቤትን ጨምሮ ሕጋዊ አካሄድን ባልተከተለ መንገድ የሚጣሉ እግዶች ካሉ አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት እንዲቻል በተቋማት መካከል ቅንጅታዊ አሰራርን መዘርጋት እንደሚያስፈልግ በውይይቱ ተሳታፊዎች እንደመፍትሄ የጠቆመ ሲሆን በጋራ እየተከታተሉ ችግሩን ማቃለል ያስፈልጋልም ተብሏል ::