የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የስራ ኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ከተማችን አዲስ አበባ የአለም የዶፕሎማቶች መገኛ፣ የአፍሪካ መቀመጫ፣ የሀገራችን መዲና እንደሆነችው ሁሉ፤ የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግም እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች በድንገት አይበቅሉም፡፡ በምኞትም አይገኙም፡፡ ከተማችንን የኢንዱስትሪ ማዕከል እናደርጋለን ስንል የፈጠራ ባለቤቶችን በማበረታት፤ የዛሬ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኝ ኢንተርፕራይዞችን ተግዳሮቶቻቸውን በመፍታት ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ እንዲሸጋገሩ በማስቻል ወደ ብልፅግና እናመራለን ብለዋል፡፡
ሀገራችንና ከተማችን የጀመሩት ሁሉን አቀፍ የለውጥ ጉዞ የሚሰምረው ምርትና ምርታማነት ሲያድግ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው ዜጎች በጥረት ማደግን የህይወት መመሪያቸው ሊያደርጉ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በንግድና በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩትም ከአላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ በመታቀብ የዋጋ ንረትን የመከላከል ሃላፊነት እንዳለባቸው ያስታወሱት ምክትል ከንቲባው ፥ በኮንስትራክሽን የደረጃ ሽግግር የሚያደርጉ ኢንተርፕራይዞች ከተማዋ በዘርፉ የምትፈልገውን ስታንዳርድ በብቃት መታጠቅ እንደሚጠበቅባቸው እና በከተማ ግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕርነሮች ባለው ውስን ቦታ ቴክኖሎጂን በመጨመር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የኑሮ ውድነትን ለመከላከል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም አሳስበዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ኢንተርፕራይዞችን ከማደራጀት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ እና በማብቃት ወደ ቀጣይ ደረጃዎች እንዲሸጋገሩ በሚያከናውነው ተግባር እስካሁን 2 ሺ 241 ኢንተርፕራይዞችን ማሸጋገር ተችሏል። እየተካሄደ በሚገኘው የ12ኛው ዙር ምረቃ 469 ኢንተርፕራይዞች ከጥቃቅን እና አነስተኛ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ደረጃ እንዲሁም ለመጀመሪያ ግዜ 12 ከመካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ ደረጃ የሚሸጋገሩ ይሆናል።
በአጠቃላይ በ12ኛ ዙር 481 የተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች እና ኢንዱስትሪዎች የሚመረቁ ይሆናል።