በመርሃ-ግብሩ ላይ የአዲሱን ስርዓተ ትምሕርት መጀመርና የተማሪዎች መማሪያ እና የመምህር መምሪያ መጻህፍት ዝግጅት ላይ ለተሳተፉ መምህራን ርእሰ መምህራንና ባለድርሻ አካላት ዕውቅናና የሽልማት አሰጣጥ ስነስርአት ተካሂዷል።
በዚሁ ስነስርዓት ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት ክረምቱን ከሞቀ ቤታችሁ ብርድና ቁር ሳይበግራችሁ የተሰጣችሁን ኃላፊነት በብቃት በመወጣት የየድርሻችሁን አሻራ ለአገር ሁለንተናዊ ግንባታና የትውልድ ስብዕና ቀረጻ ላይ ያበረከታችሁ ባለሙያዎችን ከተማ አስተዳደሩ ለልፋታችሁ እውቅና በመስጠት ያመሰግናችኋል ብለዋል
ትውልድን በሚፈለገው ደረጃ ለማነፅና አገርን በአብሮነት ቆሞ ለመገንባት የላቀ አስተዋጽኦ አለው ያሉት ከንቲባ አደነች ልክ ከዚህ ቀደም እንደታየው እዛና እዚህ ቆሞ ሁሉም በየራሱ መነፅር የሚመለከት ትውልድ የፈራበት ሳይሆን አብሮ መኖርን የሚያጠናክር የአገር በቀል እውቀትን የሚረዳ እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቶት የተሰራ ነው፡፡
ስርዓተ ትምህርቱ ወደ መሬት የሚወርደው እናንተ በሰራችሁት ስራ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች ስርዓተ ትምህርቱ ወደ መማር ማስተማር የተቀየረበት መንገድ አስተማሪ ነው ብለዋል፡፡ ሰርታችሁ አሳይታችሁናል፡፡ በዚህ ረገድ ሁላችንም በተሰማራንበት ሁሉ የየበኩላችንን ተደማሪ አሻራ ማኖር ይጠበቅብናል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
አገር የሚገነባው ሁሉም በየደረጃው የየበኩሉን ሳይሰስት ፊት ለፊት ምሳሌ ሆኖ መስራት ሲችል ነው ያሉት ይህን ይህን ስራ ለአማካሪዎች ከመስጠት ይልቅ እናንተ እንድትሰሩ መደረጉ ባለቤቶቹ ጥራቱም በገንዘብም ውጤታማ መሆን እንድንችል አድርጎናል ብለዋል ለዚህም ከንቲባ አዳነች በቀጣይ የትውልድ ስብዕና ግንባታ ላይ በምትሰሯቸው ስራዎች ሁሉ ከተማ አስተዳደሩ አብሯችሁ ይቆማል ብለዋል ።
አዲሱን ስርዓተ-ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግ በተዘጋጀው መረሀ-ግብር ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ የትምሕርት ፖሊሲና ስርዓተ -ትምሕርት የላቀ ጥራትን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ መከለሱ ይታወቃል ያሉት እኛም ከዚሁ ጋር እንዲጣጣም አድርገን ነው አዲሱን ስርዓተ -ትምሕርት ያዘጋጀነው ብለዋል ።
አዲሱ ስርዓተ -ትምህርት በአጠቃላይ የመጽሐፍት ህትመት ስራው ከአንድ ቢሊዮን ብር ባነሰ ወጪ እንዲዘጋጅ መደረጉን ጨምሮ በ17ሺ ሦስት መቶ በግልና በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ የሚደረግ ነው፡፡
30ሺ አራት መቶ 19 መምህራን አዲሱን የስርዓተ -ትምሕርት እንዲያስተምሩ ሁሉን አቀፍ ቅድመ ዝግጅት ያደረጉ መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር ዘላለም 960 መምህራን የተሳተፉበት ትምሕርት በሬዲዮ ፕሮግራም በአዲሱ ስርዓተ – ተካቶ እንዲዘጋጅ መደረጉን ከኃላፊው ማብራሪያ መረዳት ተችሏል ።
የመማሪያ መጽሐፍቶች ከመጀመሪያ ገጽ ከመግቢያው አንስቶ ተማሪዎች አካባቢያቸውንና አገራቸውን እንዲያውቁ ተደርጎ በገላጭ ምስሎችና በአገር በቀል እውቀቶች ተቃኝቶ የተዘጋጀውን አዲሱን ስርዓተ -ትምህርት ጨምሮ በምናከናውናቸው የየዕለት ተግባራት ሁሉ እየደገፏቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነችን አመስግነዋል