የከተማ አስተዳደሩ የስራ አፈጻጸምና የቀጣይ የትኩረት ነጥቦች ላይ በሚከናወነው የግምገማ መድረክ ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ አለሙ እና ም/ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ በተገኙበት ተጀምሯል።
ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት በሚቆየው የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች በሚሳተፉበት የግምገማ መድረክ የ2014 ዓ.ም የመንግስትና የፓርቲ ስራ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2015 ዓ.ም የትኩረት ነጥቦች ላይ ውይይት ይደረጋል።
በከተማዋ ከተከናወኑ በርካታ ተግባራት መካከል በጥንካሬ ትምህርት የሚወሰድባቸውን በመለየት የማስፋት እና ቀጣይነት የማረጋገጥ ሂደት ላይ ትኩረት ተደርጎ ውይይት ይደረጋል።
እዲሁም ባለፈው በጀት አመት የነበሩ እጥረቶችን እና ጉድለቶችን በመለየት የመሙላትና የእርምት መውሰድ የሚቻልበት ጉዳዮች ላይ ውይይት ይከናወናል።
ከዚህም በተጨማሪ የቀጣይ በጀት አመት የትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ለይቶ በእነርሱ ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር የከተማዋን ልማትና ዕድገት ለማፋጠን፣ መልካም አስተዳደር ችግሮችን ማቃለል፣ አንገብጋቢ የህዝብ ጥያቄዎችን መፍታት እና የህዝብ የኑሮ ጫና መቀነስ በትኩረት ይመከራል።