የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት 9 ወራት በከተማው የነበረውን አፈፃፀም ከከተማው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በጋራ ገምግሟል፡፡ በማጠቃለያውም የቀጣይ የርብርብ ማእከል የሆኑ አቅጣጫዎችም ተቀምጧል፡፡
በግምገማው በጥንካሬ የተነሱ ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል ከሰላም አኳያ የተሰሩ መልካም እና አበረታች ስራዎች ፤ከፕሮጀክት አፈፃፀም አንፃር የታዩ ጠንካራ ጎኖች ፤በውሃ በመንገዶች ላይ የታዩ መልካም እንቅስቃሴዎች፤ በዲዛይንና ኮንስትራክሽን፤ በስራ እድል ፈጠራ ፤በገቢና በትምህርት እንዲሁም በጤና ዘርፍ መልካም አፈፃፀም መታየቱ ተገምግሟል፡፡
የኑሮ ውድነቱን ለማርገብም የተደረገው ርብርብ አበረታችን እንደነበርም የተቀመጠ ሲሆን በተቋማዊ የሪፎርም ስራዎችም በርካታ ጠንካራ እንቅስቃሴዎች መደረጋቸው ተገልጧል፡፡
የከተማ አስተዳደሩም በህልውና ዘመቻው የደጀንነት ሚናውን በመወጣት ከፍተኛውን ድርሻ ወስዶ ውጤታማ ሥራ ማከናወኑን ተገልጿል::
በቀጣይ በከተማው ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫ ተብለው የተቀመጡ የአገልግሎት አሰጣጡን በከፍተኛ ደረጃ ማሻሻል ትኩረት የሚሰጠው ሲሆን የኑሮ ውድነትን ማሻሻል በተመለከተ ርብርብ የሚደረግበት ማእከል ሆኖ ይቀጥላል፡፡
የከተማዋን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ስራ እንዲሁም ሌብነትና ስርዓት አልበኝነትን ማስተካከል ትኩረት የሚሰጠው እና ህዝቡን በማሳተፍ የሚከናወን ይሆናል፡፡
የስራ እድል ፈጠራ ስራም የትኩረት ማእከል ሲሆን የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን የማጠናቀቅና አማራጭ የቤት አቅርቦት ሞዳሊቲን ማስፋትና የመፈፀም አቅም መገንባትም በዚሁ ደረጃ የሚታዩ ናቸው፡፡
ህብረተሰቡን በየደረጃው በተለያዩ አጀንዳዎች ማወያየት እና ከህዝቡ ጋር ተቀራርቦ መስራት እንዲሁም የተጀመረው የከተማ ግብርና ስራን አጠናክሮ መቀጠል እና 4ኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ ስራን ከተቋማት ጀምሮ በተደራጀ መንገድ መፈፀም የቀጣይ ጊዜያት አቅጣጫ ሆኖ ተቀምጧል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማጠቃለያው ላይ በርካታ ውጤታማ ስራዎች ባለፉት 9 ወራት ማከናወን መቻሉን ገልፀው፤ በተለይ በፀጥታና ስራ ህዝቡን የፀጥታ ስራ ባለቤት በማድረግ ጠንካራ ስራ መሰራቱን አንስተዋል፡፡ በሌሎችም ዘርፎች የታዩ መልካም ውጤቶች ይበልጥ ተጠናክረው ጉድለቶች ታርመው እንዲቀጥሉ ችግር ፈቺ አመራር መሆን አለብን በማለት ገልፀዋል፡፡ችግር መደርደር ሳይሆን ውጤት ማምጣት አለብን በማለት የገለፁ ሲሆን አመራሩ ራሱ ምሳሌ ሆኖ መምራት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
እንዲሁም ተቋም መገንባትና ተቋማዊ ቅንጅት ብሎም (system) ስርዓት መገንባት አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን ያሰመሩበት ሲሆን መልካም ልምዶችን ማስፋትም የቀጣይ በሁሉም አመራሮችና በሁሉም ተቋማት ትኩረት መሆን እንዳለበት አስምረውበታል፡፡
ም/ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው ያለን ቀሪ ጊዜ አነስተኛ በመሆኑ አመራሩ በልዩ ሁኔታ ተሯሩጦ በጊዜ የለኝም ስሜት መፈፀም እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡