የአዲስ አበባ ከተማ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የለውጥ ሃሳብ መሰረት አዲስ ገጽታ እየያዘች መሆኑን በአሜሪካ ተነባቢ የሆነው መጽሄት ዘ ኢኮኖሚስት ባወጣው ዘገባ አመለከተ።
መጽሄቱ የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ማእከል ስለሆነችው አዲስ አበባ ሰፋ ያለ ሃተታ ያስነበበ ሲሆን ከተማዋ ካለፉት አራት አመታት ወዲህ ግዙፍ የመሰረተልማት ግንባታና የገጽታ ለውጥ ላይ መሆኗን እንደታዘበ ገልጿል።
ከተማዋ ለነዋሪዎቿ መዝናኛና ልዩ ልዩ ሁነቶች መከወኛ በቂ ቦታዎች እንዳልነበራት አስታውሶ፤ ከሸገርና እንጦጦ ፓርኮች በተጨማሪ ለህዝብ አገልግሎት ክፍት የተደረጉ ማዕከላት መፈጠራቸውን አስነብቧል።
ማዕከላቱ ሰርግን ጨምሮ በርካታ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁነቶችን ማስተናገድ እንደጀመሩ ገልጿል።
አዲስ አበባ ከምስረታዋ ጀምሮ በበርካታ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ውጣ ውረዶች ውስጥ ማለፏን ያጣቀሰው መጽሄቱ ከተማዋ የጣሊያን ቅኝ ግዛትና የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም አስተሳሰብ አሻራዎችንም ማስተናገዷን ጠቅሷል።
የአውደርእይ ማዕከላትን፣ ሙዚየሞችን፣ አብያተ መጻህፍትን፣ ክፍት የተውኔት ማሳያዎችን፣ መዝናኛዎችንና መናፈሻዎችን ያካተተው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተማዋን የመለወጥ ሃሳብ ለተፈጥሮና ለእጽዋት ከፍ ያለ ትኩረት መስጠቱ ቀልብን እየሳበ እንደሆነ አስነብቧል።
“የገጽታ ለውጡ በከተማዋ ያሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ህንጻና ግቢዎች ላይ ትኩረት አድርጓል” ብሏል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ “ጥሩ ነገር የማያይ አእምሮ ጥሩ ነገር መፍጠር አይችልም” በሚል መርሀቸው መሰረት ስራዎቹ እየተተገበሩ መሆኑን የገለጸው የዘ ኢኮኖሚስት ዘገባ፤ የከተማዋ ገጽታ እንዲሻሻል የሚያደርጉ ስራዎች እውን እንዲሆኑ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተልእኮ መውሰዳቸውን ገልጿል።
ሃገሪቱ በችግር ውስጥ እያለፈች በውበት ያሸበረቁ የህዝብ መገልገያ ማዕከላትን ከመክፈት ወደ ኋላ ያላለች መሆኗን ጠቅሷል።
በአብነትም አሸባሪው ህወሃት ጦርነት በለኮሰበት ወቅት የመስቀል አደባባይ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን አንስቷል።
ግንባታዎቹ ኢትዮጵያውያን ለሃገራቸው የሚመኙት ገጽታ ማሳያዎች መሆናቸውን ገልጿል።
ለበርካታ አመታት ያለምንም ተግባር ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎች ነዋሪው ላይ ጥያቄ ሲፈጥሩ መቆየታቸውን በማስታወስ የከተማዋ ገጽታ ይበልጥ እንዲቀየር ታሳቢ ያደረገ የከተማ ዲዛይን ማእከል መከፈቱ የዘርፉን ባለሙያዎች በማቀራረብ አዳዲስ የስራ ሃሳቦች እንዲወጡ እያደረገ መሆኑንም አትቷል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ