ተመራቂዎቹ በስልጠናው ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ህዝብ የጣለባቸውን አደራ በብቃት መወጣት እንዳለባቸውም መልዕክት ተላልፏል።
*******
የአዲስ አበባ ፖሊስ የመዲናዋን ዕድገት በሁለንተናዊ መልኩ የሚመጥን የፖሊስ ተቋም ለመገንባት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ በመቀጠል ከተለያዩ የሃገራችን ክልሎች የተመለመሉ እና በሶማሌ ክልል ብርቆት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው የክልሉ የልዩ ሃይል ፖሊስ ማሰልጠኛ ስልጠናቸውን ሲከታተሉ የቆዩ የ26ኛ ዙር ምልምል የፖሊስ አባላትን ዛሬ ነሃሴ 17 ቀን 2014 ዓ/ም አስመርቋል፡፡
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የሶማሌ ክልል የፕሬዝዳንቱ ጽ/ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ዶ/ር ሁሴን ሐሺ ፣የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ቀነዓ ያደታ ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው እንዲሁም የሶማሌ ክልል እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እና የፖሊስ አመራሮች ተገኝተዋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ቀነዓ ያደታ ባደረጉት ንግግር ሀገራችን ኢትዮጵያን የውስጥና የውጭ ጠላቶች ተባብረው ለማፍረስ ቢሞክሩም በፀጥታ ሀይሉ የተቀናጀ ስራ ሴራቸው እንዳልተሳካላቸው በማስታወስ በፖሊስነት ሙያ ህዝብን ማገልገል መታደል በመሆኑ ሰላም ወዳዱን የአዲስ አበባን ህዝብ በስልጠናው ያገኛችሁትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር በታማኝነትና በቅንነት ማገልገል አለባችሁ ሲሉ ተናግረዋል ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው ፖሊስነት ከራስ ጥቅም ይልቅ የህዝብን ጥቅም በማስቀደም ህብረተሰቡን ከወንጀልና ከትራፊክ አደጋ የመከላከል ሃላፊነት የተጣለበት የተከበረ ሙያ መሆኑን በመግለፅ በከተማዋ የሚከናወኑ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የፀጥታውን ስራ አስተማማኝ በማድረግ የአዲስ አበባ ፖሊስ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል ። የሀገራችንን እና የከተማችንን ሰላምና ደህንነት የማይፈልጉ የፀረ ሰላም ሃይሎችን እኩይ ሴራ ለማክሸፍ የፀጥታ ሃይሉ እየሰራ ያለው ስራ የሚደነቅ መሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነር ጌቱ የእለቱ የምረቃ ስነስርዓት የታላቁ ህዳሴ ግድብ 2ኛው ተርባይን ሃይል ማመንጨት በጀመረበት እና የ3ኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በተጠናቀቀበት ማግሥት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል። የዕለቱ ተመራቂዎችም በህብረተሰቡ እና በፀጥታ አካላት ትብብር በዘላቂነት የቀጠለውን የአዲስ አበባ እና የነዋሪዎቿን ሰላም ለመጠበቅ ተጨማሪ አቅም መሆናቸውን ተረድተው የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡ ለስልጠናው መሳካት ድጋፍ ላደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እና የማሰልጠኛው ማህበረሰብ እንዲሁም የአዲስ አበባ ፖሊስ አካዳሚ መምህራን እና አሰልጣኞች ኮሚሽነር ጌቱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የሱማሌ ክልል የፕሬዝዳንቱ ጽ/ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ዶ/ር ሁሴን ሐሺ ባስተላለፉት መልዕክት የአዲስ አበባ ከተማ እና የሶማሌ ክልል መልካም ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀው በቀጣይ ለሚኖሩ መሰል ስልጠናዎች የክልሉ መንግስት በፀጥታውም ሆነ በሎጀስቲክስ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ አካዳሚ ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር ብስራት ታደለ ባደረጉት ንግግር ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የአዲስ አበባ ፖሊስ የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን በማከናወን የከተማችንን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመቀናጀት እየሰራ እና ፖሊስ አካዳሚውም ሀገራቸውንና ህዝባቸውን ለማገልገል ዝግጁ የሆኑ አዳዲስ የፖሊስ አባላትን እያፈራ እንደሚገኝ ገልፀው የ26ኛ ዙር ምልምል የፖሊስ ተመራቂዎችም በክፍልም ሆነ በመስክ የተሰጣቸውን ስልጠና በብቃት የተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
ያነጋገርናቸው የዕለቱ ተመራቂዎች በሰጡት አስተያየት በመስክም ሆነ በክፍል ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየርና የነባሩን የፖሊስ አመራርና አባላት መልካም ተሞክሮዎችን በመውሰድ ህዝብ እና መንግስት የጣለባቸውን አደራ በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡