የፓሊስ አባላት የህግ በላይነትን ለማስጠበቅ በሚያከናውኑት የትኛውም አይነት እንቅስቃሴ የሰው ልጆች ሰብዓዊ መብቶችን አክብሮ በማስከበር ህጋዊ አግባብ መሆን እንዳለበት የአ/አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 7 ሰሜን ማዘጋጃ ጋበር ሆቴል በሚባል አካባቢ ሰኔ 8 ቀን 2014 ዓ/ም ከቀኑ 5 ሰዓት ላይ በክፍል ውስጥ ርንቺት ተኩሶ ከት/ቤት ውስጥ አምልጦ የሄደ አንድ ተማሪን አራት የፖሊስ አባላት ተከታትለው በመያዝ የድብደባ ወንጀል ፈጽመውበታል፡፡
ህገ- ወጥ ድርጊቱ እንደተፈፀመ ፖሊስ በደረሰው መረጃ እና ባደረገው ማጣራት ድል በር 2ኛ ደረጃ በሚባል ት/ቤት የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ነው በሚል ፕሮግራም ላይ በክፍል ውስጥ በተደረገ ዝግጅት አንድ ተማሪ ርችት እንደተኮስ እና በትምህርት ቤት ውስጥ ርችት መተኮሱ ሌሎች ተማሪዎችን እንደረበሻቸው ለፖሊስ መረጃ ይደርሰዋል፡፡ በእለቱ ድርጊቱን ፈፅሟልየተባለው ተማሪ ከት/ቤቱ ቅጥር ግቢ እንደወጣ የተነገራቸው 4 የጉለሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ አባላት ክትትል በማድረግ ሰሜን ማዘጋጃ ጋበር የሚባል ሆቴል አካባቢ ተማሪውን ይዘውት ተገቢ ያልሆነ ድብደባ ፈፅመውበታል፡፡
የአ/አበባ ፖሊስ እንዳስታወቀው ፖሊስ መረጃው ካደርሰው በኋላ ተጠርጣሪ የፖሊስ አባላቱን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራይገኛል ፡፡
በማነኛውም ሁኔታ ውስጥ የህግ አስከባሪነት መነሻው ህግን ማክበር መሆኑን ያስታወቀው ፖሊስ የዜጎችን ህጋዊ መብት በሚፃረሩ የፖሊስ አባላት ላይ የሚወሰደውን ዕርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥልና በማንኛውም ሁኔታ ህገወጥ ተግባራት ሲፈፀሙ ህ/ሰቡ በያገባኛል ስሜት የሚሰጠውን መረጃ አጠናክሮ እንዲቀጥል ፖሊስ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡