መስከረም 07 ቀን 2015(ኢዜአ) የጉባኤው የበላይ ጠባቂ አባቶች በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገኘት የግንባታውን ሂደትና አሁናዊ ሁኔታ ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸው ወቅት አዲሱ 2015 ዓ.ም ለኢትዮጵያ የሰላም፣ የተስፋና የአንድነት እንዲሆን ተመኝተዋል።
ለኢትዮጵያና ለግድቡ ሰራተኞች በስፍራው ፀሎት በማድረግ ግድቡን ባርከዋል።
በጉብኝቱ የእያንዳንዱ ቤተ እምነት አባቶች መልክት ያስተላለፉ ሲሆን ሶስተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁና አሁን ለደረሰበት ደረጃ በመድረሱ ለኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ ያላችሁ መልክት አስተላልፈዋል።
የግድቡ ግንባታ ግብጽና ሱዳንን ጨምሮ ታችኞቹን የተፋሰስ አገራት ህዝብ የማይጎዳ መሆኑን ከባለሙያዎች ገለጻ መረዳታቸውን አባቶቹ ገልፀዋል።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሁላችንም የጋራ ሃብትና የነገ ተስፋ በመሆኑ ትዮጵያውያን ሰላምና አንድነታቸውን በማስጠበቅ ለግድቡ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልክት አስተላልፈዋል።
የጉባኤው ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ፤የኢትዮጵያ የአንድነትና ህብረት ተምሳሌት የሆነውን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በአዲስ አመት መጀመሪያ በመጎብኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን ለማጽናት በተለያዩ ግንባሮች መስዋዕት እየተከፈለ ሲሆን በዚህም ስፍራ የአገራቸን እድገትና ብልጽግና እውን እንዲሆን ሌት ተቀን ያለመታከት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ለአገር ብልጽግና፣ ልማትና አንድነት ምሳሌ የሆነውን ግድብ ከዳር ለማድረስ ጥረት ማድረግ አለብን ነው ያሉት