የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል ሰኞ ጥቅምት 7 ቀን 2015 ዓ.ም “ሰንደቅ ዓላማችን የብዝሃነታችን መገለጫ የሉዓላዊነታችን ምሰሶ ነው!” በሚል መሪ ቃል ይከበራል፡፡
ዜጎች ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅርና ብሔራዊ ስሜት ለሰንደቅ ዓላማ በሚሰጡት ክብር ይገልፃል፤ በእኛ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ሰንደቅ ዓላማ ትልቅ ስፍራ ያለው ነው፤ ለሰንደቅ ዓላማ የምንሰጠው ክብርና ፍቅር ከእናት አባቶቻችን በክብር ወርሰን በክብር ለቀጣዩ ትውልድ የምናስተላልፈው በልባችን ውስጥ ታትሞ የሚቆይ የብዝሃነታችን፣ የአንድነታችንና የሉዓላዊነታችን መገለጫ ታላቅ ሀገራዊ እሴት ነው፡፡
ሰንደቅ ዓላማችን የመስዋዕትነት፣ የሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት፣ የስነ-ልቦና፣ የፖለቲካ ታሪክ፣ የአብሮነትና የብሔራዊ መግባባት መገለጫ አርማ ምልክታችን በመሆኑ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለሰንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር መስጠት፤ የማክበርና የማስከበር ሃላፊነትና ግዴታ አለበት።
የብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 863/2006 (እንደተሻሻለው) አንቀጽ 2 መሰረት በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ መጀመሪያ ሳምንት ሰኞ እንደሚከበር ተደንግጓል፡፡
የብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል በተለያየ መልኩ በየዓመቱ እየተከበረ አስራ አራት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በያዝነው ዘንድሮ ዓመትም “ሰንደቅ ዓላማችን የብዝሃነታችን መገለጫ የሉዓላዊነታችን ምሰሶ ነው!” በሚል መሪ ቃል ሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታን በዋጀ ለ15ኛ ጊዜ የፊታችን ሰኞ ጥቅምት 7 ቀን 2015 ዓ.ም በፌደራል፣ በክልሎችና በሁለቱም የከተማ አስተዳደር ከተሞች ከሰንደቅ ዓላማ መርሆዎች ጋር ተገናዝቦና ሀገራዊ ሪፎርሙን በሚያስቀጥሉ ውይይቶች ታጅቦ በየተቋማቱ ይከበራል፡፡
የውስጥ ቅጥረኛ ተላላኪዎቻቸውን ይዘው በቅርብም ከሩቅም ያሉ የውጭ ጠላቶቻችን አቅደውና ተናበው ብሔራዊ አንድነታችንን እና ሉዓላዊነታችንን አደጋ ላይ ለመጣል እየሰሩ ባሉበት በዚህ ወቅት የሰንደቅ ዓላማ ቀን መከበሩ ለሕብረብሄራዊ አንድነታችን መጠናከር፣ ለሉዓላዊነታችን መከበርና ይበልጥ ብሔራዊ መነቃቃትን ለመፍጠር ትልቅ ትርጉም የሚኖረው ሲሆን ለሀገር ክብርና ጥቅም ሁላችንም እንደዜጋ የበኩላችንን ለመወጣት በሰንደቅ ዓላማ ፊት ዳግም ቃላችንን የምናድስበት ዕለት ይሆናል፡፡
ስለሆነም የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ በዓሉ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሪነት በመላው ሀገሪቱ የሚከበር ሲሆን በፌደራል የመንግስት ተቋማት፣ በክልሎችና በሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች፣ በመከላከያ ሰራዊት ካምፖች እንዲሁም በኢምባሲዎችና የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች በተመሳሳይ ሰዓት ከረፋዱ 4፡30 ላይ ሰንደቅ ዓለማ በመስቀልና በሰንደቅ ዓላማ ፊት ቃለ መሐላ በመፈፀም ስነ-ስርዓት እንዲሁም በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ የሚከበር ይሆናል፡፡