ፕሮጀክቶቹን ያስጎበኙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት ምክር ቤቱ የአዲስ አበባችን የለውጥ እንቅስቃሴን ጨምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ የብልጽግና ጉዟችንን ለማሳለጥ በክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ሃሳብ አፍላቂነትና የተግባር አመራር ሰጪነት በሁሉም ረገድ የምናከናውናቸውን የልማት ስራዎች እየተከታተለ እንዲደግፈንና ማስተካከል የሚጠበቅብንን ጉዳዮች በማመላከት የበኩሉን አሻራ እንዲያኖር እንፈልጋለን ብለዋል ።
ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች ስንል በነዚህ ተጨባጭ የልማት ስራዎቻችን ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች ሩቅ ማለም ወይንም አርቆ መመልከት የሚል ስያሜ የሰጠነው ከማዘጋጃ ቤት እስከ ለገሀር ያለው የጎዳና ማስዋብ ሥራ ፤በቀላሉ የምንጓዝበትን አዲስ እይታ ፍንትው አድርጎ እንዲያስመለክት ተደርጎ የተገነባ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የከተማችንን የወደፊት ዕድገትና ተስፋ የማይመጥን ነበር ያሉት ከንቲባዋ ዛሬ ላይ ከማዘጋጃ ቤት እስከ መስቀል አደባባይ ባከናወናቸው የአካባቢ ገጽታን የማስዋብ ስራዎች ዜጎች ሲያሻቸው የሚናፈሱበትና የሚያነቡበት ሥፍራ ማድረግ ችለናል ።
የዓድዋን ታሪክ እዚህ ቦታ ሕያው አድርገን ለማስቀም እንዲቻል ገድሉን ሕያው አድርገው የሚያሳዩ ማስረጃዎቻችንን የዘርፉ ሙሁራን እያሰባሰቡ ይገኛሉ ያሉት ከንቲባ አዳነች የፓርኩ ዲዛይን የአባቶቻችንን የዓድዋ ተራራ ውጣ ውረድ እንዲያሳይ ተደርጎ እየተገነባ ያለ መሆኑን አስታውቀዋል።