በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ ተቋሙ በሰው ሀይል፣ በአደረጃጀት፣ በቴክኖሎጂና በአሰራር ለማዘመን እያካሄደ ያለውን የሰራ እንቅስቃሴ በዛሬው እለት ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
አቶ ጥራቱ በየነ ኮሚሽኑ የተቋቋመበት ተልእኮ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በሰውና በንብረት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርሱ አስቀድሞ የመከላከልና ከደረሰም በፍጥነት ጉዳቱን ለመከላከል የሚያስችል እንደመሆኑ ይህንኑ በብቃትና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመወጣት የተጀመረው የሪፎርም ስራ ተስፋ ሰጭ ነው ሲሉ ተናግረዋል ።
በጉብኝቱ ወቅት በተለይም ምቹ የስራ አካባቢን የመፍጠርና ግቢውን ፅዱና ውብ በማድረግ ረገድ የተከናወኑ ስራዎች አበረታች እንደሆኑም አቶ ጥራቱ በየነ አስገንዝበዋል።
አቶ ጥራቱ በየነ ከዚህ ጋር በተያያዘም በሪፎርም ስራው በተለይ ከህንፃ እድሳትና የዲዛይን ስራ፣ከቴክኖሎጂ ዝርጋታ፣ ከሰራተኞች ማደሪያና የጥሪ ማዕከል አንፃር ወደ ተግባር ከመግባት አኳያ ከጊዜ አጠቃቀም ጋር ዉስንነት ያለ በመሆኑ ስራዎችን በእቅድና በቅደም ተከተል ፈጥኖ ማጠናቀቅ እንደሚያስፈልግ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
ሪፎርሙን ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ መምራት እንዲቻልም የጥናትና ዲዛይን ስራ እንዲፋጠን፣ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ስራዎች በአፋጣኝ እንዲጠናቀቁ፣ ሪፎርሙም ወደ ዘጠኙ ቅርንጫፎችም በአስቸኳይ ወርዶ እንዲተገበርም አቅጣጫ ተቀምጧል።