በመዲናችን አዲስ አበባ በጠቅላይ ሚኒስትር ሃሳብ አመንጪነት ተገንብቶ ወደ ስራ የገባውን የአብርኾት ቤተ መፃህፍት በመፃህፍት ለማደራጀት በቀረበው ሃገራዊ ጥሪ መሰረት የኦሮምያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በዛሬው እለት ከ20ሺህ በላይ መፃህፍትን ለከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አስረክቧል፡፡
ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በመፅሃፍ ርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት የአብርሆት ቤተ-መፅሀፍት በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሀሳብ አመንጪነት የስራ ክትትልና መመርያ የተሰራ አንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ1.1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የገነባው ቤተመፅፍት ነው ብለዋል።
የአብርሆት ዋናው አላማው ኢትዮጵያን በእውቀት ብርሃን እንድትደምቅ ማድረግ ፤ በእወቀት በበለፀገ ትውልድ የኢትዮጵያ ብልፅግና እንዲሳካ በማሰብ የተገነባ ቤተመፅሃፍት ነው ሲሉም ገልፀዋል።
ይህንን የምናሳካው ራሳችንን ስናውቅ ነው ያሉት ከንቲባዋ አገር በቀል እውቀትና ባህላችንን ይበልጥ ስንረዳ ይበልጥ ስንተዋወቅ እና ስንቀራረብ ነው ብለዋል፡፡
ይህ ቤተመፃህፍት በምስራቅ አፍሪካ ትልቁ ቤተመፃህፍት ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች ከ1.5 ኪሎሜትር በላይ የሚረዝም የመፃህፍት መደርደርያ አለው፡፡ በተለያዩ የውጪ መፃህፍትም ቢኖሩትም የውጪ መፅሃፍት ክምችት ብቻውን በቂ አይደለም በአገር ቋንቋዎች የተፃፉ የኢትዮጵያን ምንነት የኢትዮጵያን እውቀቶች የሚያካፍሉ መፃህፍትምያስፈልጉናል ብለዋል፡፡
አንድ አብርሆት ሳይሆን ብዙ አብርሆቶች ያስፈልጉናል !! የከተማ አስተዳደሩ በሁሉም ክ/ከተሞች ቤተመፅሃፍቶችን የማስፋፋት ስራ ይሰራል በቅርቡ በንፋስ ስልክ ላፍቶ የተሰራው ቤተመፃህፍት ለዚህ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ስጦታውን በክልሉ ስም ያበረከቱት በኦሮምያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ የሆኑት አቶ አብዱላኪም ሙሉ በበኩላቸው በኦሮምያ የዜግነት ኢኒሼቲቭ አማካኝነት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትሎ ከሁሉም አካባቢዎች የመፅሃፍት ማሰባሰብ ሲካሄድ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
መፅሃፍቶቹም የተለያየ ይዘት ያላቸው መሆኑን አንስተው ኢትዮጵያውያን ባህላቸውንና ማንነታቸውን እንዲያውቁ የንባብ ባህል ሊዳብር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡