የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ2014 በጀት አመት መጀመርያ አነስቶ ወይም ባለፉት 9 ወራት ብቻ በተጎሳቆለ ቤት የሚኖሩ ዜጎችን አኗኗር ለመቀየር በሚያደርገው ጥረት 3000 ቤቶችን በማደስ ነዋሪዎችን ከመንገላታት መታደግ ችሏል፡፡
በዚሁ ፕሮግራም አስተዳደሩ በ2013 መጨረሻ በቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ 8 የልቤ ፋና ትምህርት ቤት አካባቢ 35 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃና ለሚኖሩ አባወራዎች መኖርያ ቤት እንደ አዲስ በአራት ዘመናዊ ብሎኮች የመገንባት ስራ አስጀምሮ ነበር፡፡
ይህ ግንባታ ያለበትን ደረጃ ስንመለከት ከአራቱ ህንፃዎች ውስጥ አንዱ ሙሉ ለሙሉ ያለቀ ሲሆን ሁለተኛው የስኬለተን ስራው ተጠናቋል እንደሁም ሶስተኛውና አራተኛው ቁፋሮና መሰረት ስራ ላይ ይገኛሉ፡፡
ይህ ስራ አስተዳደሩ ሲያከናውናቸው ከነበሩ ሌሎች ፈጣን ግንባታዎች አንፃር ወደ ኋላ የዘገየበት ምክንያት ስንመለከት አንድ ግለሰብ ቦታውን አስመልክቶ ባቀረበው የፍርድ ቤት ክርክር እና እግድ ነው። (ከስር እግዱ ተያይዟል)
በዚህ ምክንያት ለ9 ወራት በክርክር ሂደት ስራው እንዲጓተትና ነዋሪዎቹም አብላጫዎቹ በትምህርት ቤት ውስጥ እንዲቆዩ ሶስት አባወራዎች ደግሞ አስተዳደሩ ቤት ተከራይቶ እስካሁን አቆይቷቸዋል፡፡
ሆኖም ግን ሲጠናቀቅ 80 አባወራ እንዲይዝ ተደርጎ እየተሰራ ያለው ይህ ግንባታ ከ9 ወራት የፍርድ ቤት እግድ በኋላ በአሁን ሰአት ለግለሰቡ ተተኪ ቦታ ተሰጥቶት ወደ ስራ የተገባ ሲሆን ፕሮጀክቱ በፍጥነት እየተከናወነ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅና ለነዋሪዎች የሚተላለፍ ይሆናል፡፡
ነገር ግን በአንዳንድ ሚድያዎች ከተከናወኑ መልካም ስራዎች በላይ ይህ ከአቅማችን በላይ በሆነ ምክንያት የተፈጠረውን ችግር በማራገብ የተሳሳተ ገፅታ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ተገቢ አለመሆኑን አስተዳደሩ ያምናል፡፡
አስፈላጊ መረጃዎችን ከአስተዳደሩ ጋር ቀርቦ መጠየቅ እና ትክክለኛ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ማድረስ የሁላችንም ሃላፊነት የሚሰማን ዜጎች ተግባርም ሊሆን ይገባል፡፡