ከተጀመረ 4 አመታት በላይ ያስቆጠረው የካራ ኮተቤ መንገድ እስከ ሰኔ 30 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ ፕሮጀክቱን በጎበኙበት ወቅት ገልፀዋል፡፡
መንገዱ በዋነኛነት በህብረተሰቡ ጥያቄ መሰረት የዲዛይን ለውጥ በመደረጉ፣ ከዚህ በፊት የነበረው ተቋራጭ የውል ጊዜውን አጠናቆ በመዉጣቱ እና የኮንስትራክሽን ዋጋ በየጊዜው በመጨመሩ ምክንያት ከተያዘለት ጊዜ ለመዘግየቱ የሚጠቀሱ ምክንያቶች መሆናቸውን አቶ ጥራቱ የገለፁ ሲሆን አሁን ላይ በከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ተሰጥቶት ክትትል በመደረጉ እስከ ሰኔ 30 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የቀረው መንገድ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፈት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
አጠቃላይ መንገዱ 6 ኪሎ ሜት ርዝመትና 30 ሜትር ስፋት ያለው መሆኑና ከ5 ኪሎ ሜትር በላይ ያለው መንገድ ሙሉ በሙሉ በመጠናቀቁ እንዲሁም የቀረው 200 ሜትር መንገድ በሰቤዝ ደረጃ በማጠናቀቅ ሌሎች የቀሩ ትንሽ ስራዎች እስኪጠናቀቁ ድረስ የቀኙ መንገድ እስከ ሰኔ 30 ባለው ጊዜ ውስጥ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳሬክትር የሆኑት ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ ገልፀዋል፡፡
መንገዱ በተባለለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሲሆን የነበሩ የትራፊክ መጨናነቆችን እና የነዋሪዎችን እንግልት ይቀርፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡