የወላይታ ልማት ማህበር የቀጣይ 20 ዓመታት የልማት እቅድ ማብሰሪያ መርሐግብር በአዲስ አበባ ከተማ ወዳጅነት አደባባይ ተካሂዷል ።
“የወላይታ ልማት ማህበር አስተዋጽኦ ለወላይታ ብሎም ለኢትዮጵያ ብልጽግና የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው “በሚል በተካሄደው የማብሰሪያ መርሐግብር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደገለፁት የወላይታ ህዝብ በከተማዋ በስራ ወዳድነት እና በታታሪነቱ የሚታወቅ ነው ብለዋል።
የወላይታ ህዝብ በተለያዩ ጊዜያት ሀገራዊ ጥሪ በቀረበ ጊዜ አሻራውን የሚያኖር ፣በሀገር ግንባታ እና በኢትዮጵያ አንድነት የማይደራደር ፤አብሮ መኖርን በማስቀደም ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል ።
እኛ ኢትዮጵያዊያን በጋራ ቆመን ለጋራ እድገት ከሰራን ወቅታዊ ፈተናዎች አያስቆሙንም ያሉት ምክትል ከንቲባዋ ተስፋን ሰንቀን ወደፊት እያየን እጅ ለእጅ ተያይዘን ማደግ እና መበልፀግ ይገባናል ብለዋል።
የወላይታ ልማት ማህበር በአዲስ አበባ ከተማ የወላይታ ባህል እና ትውፊትን ለማሳደግ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ የከተማ አስተዳደሩ የባህል ማዕከል መገንቢያ ቦታ ማዘጋጀቱን ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል ።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር እንድሪያስ ጌታ በበኩላቸው የልማት ማህበሩ ሶስተኛውን እቅድ አጠናቆ በቀጣይ 20 ዓመታት ተግባራዊ የሚሆን የስምንት ቢሊዮን ብር የልማት እቅድ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል ።
በቀጣይ 20 ዓመታት እቅድ በሰው ሀብት ልማት ፣በትምህርት ማስፋፋት እና የወላይታ ባህል እና ቋንቋ ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል ።
በመርሐግብሩ ላይ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኤርካቶ፣የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር እንድሪያስ ጌታ ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች እና በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የዞኑ ተወላጆች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳፈትዋል።