ለሁለተኛ ዙር ከከተማ ማዕከል እስከ ወረዳ በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና መድረክ ተጠናቀቀ
በአዲስ አበባ ከተማ “መፍጠንና መፍጠር፤ የወል እውነቶችን የማፅናት ቀጣይ የትግል ምዕራፍ” በሚል ከከተማ ማዕከል እስከ ወረዳ በየደረጃው ለሚገኙ 4162 አመራሮች ባለፉት አራት ቀናት ሲሰጥ የነበረው የስልጠና መድረክ በዛሬው ዕለት ተጠናቋል።
የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮችም በቪዲዮ ኮንፈረንስ የማጠቃለያ ሀሳቦችና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን ሰጥተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት አመራሩ ለሀገረ መንግስት ግንባታ ተግዳሮት የሚሆኑ ጉዳዮችን በማረምና በማስተካከል ብሔራዊ መግባባትን ሊፈጥሩ የሚችሉ ስራዎችን በመስራት የወል እውነቶችን ማጽናት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ከውስጥ ያለንን አቅማችንን በሚገባ በመጠቀም መፍጠንና መፍጠር ይገባናል ያሉት ከንቲባ አዳነች መበተንና መለያየት አቅማችንን ስለሚያሳንሱ ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በመጠበቅ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ማድረግ እንደሚገባም አስረድተዋል።
የዓለም ተለዋዋጭ ሁኔታ አጠቃላይ በምንሰራቸው ስራዎች ውስጥ የራሱ ተጽዕኖ እንዳለው ያስረዱት ከንቲባዋ በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ በመሆን በርካታ ሀገራዊ ለውጦችን ማስመዝገብ መቻሉን አስረድተዋል።
በተጨማሪም ሰላምና ጸጥታችን ላይ ብዙ ጊዜ ችግር የሚገጥመን የወል እውነቶችን አጥብቀን ባለመያዛችን ነውና የወል እውነቶችን በማጽናት፤ ልዩነቶችን በንግግር በመፍታት ሰላማችንን ማስቀጠልና ማጽናት አለብን ሲሉ ከንቲባዋ ተናግረዋል።
የከተማዋ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው ባለፉት አራት ቀናት ሲሰጥ የነበረው ስልጠና በአመራሩ ዘንድ ተግባቦትን የፈጠረ እና ለቀጣይ ስራ ያነሳሳ እንደነበር አስረድተዋል ።
አሁን ባለንበት ሁኔታ ሀገራችን ጠንካራ ፓርቲ፤ ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት ወቅቱ የሚጠይቅበት ጊዜ በመሆኑ እንደ ፓርቲ ለህዝብ ከገባነው ቃል አንፃር ኃላፊነታችን ከፍ ያለ ነው ሲሉ አቶ ሞገስ ተናግረዋል።
ህብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያን ለመገንባት ጠንካራ የሆነ ፓርቲ መገንባት ይጠይቃል ያሉት አቶ ሞገስ ለዚህም ደግሞ ነባራዊ ህልውናዊ፣ አለማዊና ሀገራዊ ሁኔታን በማወቅና በመተንተን የሀሳብ ጥራት በመያዝ እና ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር፣ የውስጠ ፓርቲ አንድነትን በማጠናከር እንዲሁም የተገኙ ውጤቶችን በማጽናት ጠንካራ ፓርቲ መገንባት እንደሚቻል አስረድተዋል።
የምናልመውን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማሳካት የፓርቲ መሪነትን ማረጋገጥ ይገባል ያሉት ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ አመራሩ የውስጠ ፓርቲ ስራዎችን በማጠናከር የማይናወጥ ተቋም መፍጠር እንደሚገባው አስረድተዋል።
ተናጠላዊ እውነታዎችን ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በሚፈጠረው መድረኮች ላይ በማስተናገድና መፍታት የሚቻልበት ሁኔታ በመፍጠር የወል እውነታዎችን ማረጋገጥ እንደሚገባ አቶ ጃንጥራር ተናግረዋል።
በስልጠና መድረኩ ላይ የተሳተፉ በየደረጃው ያሉ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ስልጠናው ቀጣይ ለሚኖሩ ተልዕኮዎች መፍጠንና መፍጠር የሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ እንደተፈጠረላቸው እና በአብሮነት፣ በትብብር፣ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ሊያረጋግጥ በሚችል መልኩ ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችል መድረክ እንደነበር አመላክተዋል።