በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 03 ዋና ስራ አስፈጻሚና ምክትላቸው በመስሪያ ቦታ አሰጣጥ ተደራድረው የሙስና ጉቦ ሲቀበሉ እጅ ከፈንጅ መያዙን የጉለሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
የጉለሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ረ/ኮሚሽነር ፋሲካ ፈንታ እንደገለጹት በጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 03 ከስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ብሎክን መሰረት በማድረግ የተፈጠረ የስራ እድል ላይ ከተጠቃሚ ወላጅ ጋር የተሻለ የመስሪያ ቦታ በጉንድሽ የመስሪያ ቦታ እናሰጣለን በማለት የተጠቃሚዋን ወላጅ አባት ብር ካልሰጠኸን ልጅህን ከስልጠና እናወጣታለን፣ የስራ እድልም አይፈጠርላትም በማለት ወላጅ አባቷን በማስፈራራት ልዩ ስሙ 6 ኪሎ አከባቢ ልዩ አዲስ ሆቴል 50,000 (ሀምሳ ሺህ ብር) ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል።
እጅ ከፍንጅ የተያዙት ግለሰቦች 1ኛ የጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 03 ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አያናው አስራት እና 2ኛ የወረዳው ምክትል ስራ አስፈጻሚና የስራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ እዮብ አፈወርቅ 5000 ብር በዛሬ እለት ከቀኑ 10:30 ሰዓት ሲቀበሉ ክትትል በማድረግ በጸጥታ ሃይሎች እጅ ከፍንጅ ተይዘው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ገብተው ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል።
የክ/ከተማው ፖሊስ መምሪያ ይህንን አይነት ፍፁም ተገቢ ያልሆነ ተግባር ኮንነው ባስተላለፉት መልዕክት፣ የከተማችን ነዋሪ በየትኛውም የመንግስት ተቋም ለሚሰጡ አገልግሎቶች ሙስና ለመቀበል የሚጠይቁና የሚቀበሉ ማናቸውንም አካላት በመጠቆም ተባባሪ እንዲሆን ጥሪ አስተላልፈዋል።
የከተማችን ነዋሪ በዚህ አጊጣሚ መሰል ነገር በሚገጥመው ወቅት ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት ለህግ አስከባሪ አካላት የተለመደ ትበብሩን እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል።