የአዲስ አበባ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የውሃ ብክነትን በመቀነስ የውሃ አቅርቦቱን እና ስርጭቱን ማስተካከል የሚያስችል ስምምነት ማያ ኮርፖሬሽን ከተባለ የሉክዘንበርግ ድርጅት ጋር ተፈራርሟል ፡፡
የከተሞች ውሃ አቅርቦት እና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ሁለተኛው ምዕራፍ አካል የሆነው ይህ ስምምነት፤ አጠቃላይ ወጪው 800 ሚሊየን 487 ሺህ 107 ብር ሲሆን በአራት አመት ከ2 ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ በስምምነቱ ተገልጿል ፡፡
ስምምነቱ በጉርድ ሾላ እና ለሚ ኩራ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በተለዩ 25 ቀጠናዎች ማለትም በየካ አባዶ፣ የካ አያት፣ ፋኑኤል፣ ቦሌ አያት እና ቦሌ አረብሳ አከባቢ በሚገኙ የውሃ ስርጭት መስመሮች ላይ የዲዛይን ስራ በመስራት እያጋጠመ ያለውን የውሃ ብክነት በመቀነስ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ነው ተብሏል ፡፡
የተፈረመው ስምምነት አፈፃፀምን መሰረት ያደረገ (Performance based contract) ሲሆን ከ37 ሺህ 500 በላይ ደንበኞች በሚገኙበት አከባቢዎች ያረጁ የውሃ መስመሮችን፣ የውሃ ቆጣሪዎችንና መገጣጠሚያዎችን በመቀየር፣ የደንበኞችን መረጃ በማዘመን እና የዕውቀት ሽግግርን በማድረግ የውሃ ስርጭት መረቡን የሚስተካክል እና ሲባክን የነበረውን ንፁህ የመጠጥ ውሃ የሚያድን መሆኑን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ገልጿል ፡፡