የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ አመራሮች “መፍጠንና መፍጠር” በሚል መሪ ሀሳብ የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ዙሪያ የውይይት መድረክ እያከናወኑ ይገኛል
የውይይት መድረኩ ያስጀመሩት የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል እንደገለጹት “መፍጠንና መፍጠር” አስፈላጊነት ላይ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ተወያይቶ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በየደረጃው ላለው አመራር ግልፀኝነትን በመፍጠር ወቅቱ የሚፈልገው አመራር ለመፍጠር ያለመ የውይይት መድረክ እንደሆነ ተናግረዋል።
የዚህ የውይይት መድረክ ዋነኛ ዓላማ ዓለም አቀፋዊ፣ ቀጠናዊና ሀገራዊ ጉዳዮች በስፋት የሚዳሰሱበት እንዲሁም ባለፉት ጊዜያት የነበሩ ስኬቶችና ተግዳሮቶችን ተገንዝቦ ስኬትን ለማላቅ ተግዳሮቶችን ወደ ዕድል ለመቀየር ስንቅ ለመያዝ እና የላቀ ዝግጁነትን ለመፍጠር ያለመ እንደሆነ ወ/ሮ ሙፈሪያት ገልጸዋል።
የብልፅግና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የከተማዋ ብልፅግና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው አመራሩ በውይይት መድረኩ በመረጃ፣ በእውቀት፣ በትንታኔ ላይ የተመሠረተ አቅም እንዲያገኝና በአቅሙ ልክ ኃላፊነቱን መወጣት የሚያስችል የጋራ ተግባቦት እና ግንዛቤ መፍጠር የሚያስችል መድረክ እንደሚሆን ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ የውይይት መድረክ ከሌላ ጊዜ ለየት የሚያደርገው በፌደራልና በክልሎች ያሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አመራሮች የሚያወያዩት መሆኑ ለየት የሚያደርገው መሆኑን የተናገሩት አቶ ሞገስ ከከተማ አስተዳደሩ ውጭ ያሉ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አመራሮች ማወያየታቸው በፓርቲያችን ውስጥ የበለጠ አንድነትን፣ አብሮነትን፣ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ትልቅ መደላድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ የከፍተኛ አመራሩ የውይይት መድረክ ለተከታታይ አራት ቀናት እንደሚከናወን እና መድረኩ እንደተጠናቀቀም በቀጣይ በየደረጃው ያሉ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችን የማወያየትና የፓርቲያችንን አቅጣጫ ወደ ሁሉም አባላትና ህዝቡ ሊደርስ የሚችልበት ሁኔታ እንደሚፈጠር አቶ ሞገስ ተናግረዋል።