ወደ ብልጽግና የምናደርገው ጉዞ የተሣለጠ የሚሆነው በዋናነት በውስጣዊ ዐቅማችን ላይ ከተመሠረተ ነው። ውስጣዊ ዐቅማችን ማለት የሕዝባችን ዐቅም፣ የሀገራችን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ሀብት እንዲሁም የአዲሱ ትውልድ የፈጠራ ክሂሎት ናቸው።
በአስቸጋሪ ፈተናዎች ውስጥ እያለፍን እንኳን ችግር ተቋቋሚ ኢኮኖሚ ሊኖረን ችሏል። የዚህ ዋነኛ ምክንያቱ በመጠኑም ቢሆን ያሉንን ውስጣዊ ዐቅሞች አሟጠን ለመጠቀም መነሣታችን ነው። ከየትኛውም ወገን የሚሰጠን ድጋፍ በውስጣዊ ዐቅማችን ላይ ተጨማሪ እንጂ ዋና የዕድገት ምንጭ ሊሆን አይችልም።
ውስጣዊ ዐቅማችንን ተጠቅመን ወደ ብልጽግና የምናደርገው ጉዞ ከዕንቅፋቶች የጸዳ አይደለም። የኢኮኖሚ አሻጥር፣ ሌብነትና ምርት ሥወራ ዋነኞቹ ፈተናዎቻችን ሆነዋል። ወደ ውጭ መላክ የሚገባውን ምርት መደበቅ፣ ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሬ ዝውውርና መሬትን በአሻጥር መውረር በቆራጥነት ፈጣን ርምጃ ልንወስድባቸው የሚገቡ የብልጽግና ዕንቅፋቶች ናቸው።
በቀጣይ ፈተናዎችን የሚሻገር ኢኮኖሚ ለመገንባት እንድንችል ሁለት መልክ ያሉት ትግል ያስፈልገናል። ማጥፋት እና ማልማት።
የኢኮኖሚ አሻጥሮችን፣ ሌብነትንና ምርት ሥወራን ለማጥፋት የሁላችንንም ወሳኝ ትግል ይፈልጋል። በሌላ በኩል ደግሞ ገቢን የመጨመርና ወጪን በከፍተኛ ሁኔታ የመቀነስ የልማት ትግል ይጠበቅብናል።
እነዚህ ሁለቱ የትግል መስኮች በራሳችን ፖሊሲና በራሳችን ዐቅም ማደግ እንድንችል ያስችሉናል። የዕድገታችን ቁልፍ በእጃችን ነውና።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ.ር)