በትናትናው እለት ማለትም መስከረም 26 ቀን 2015 ዓ.ም በከተማ አስተዳደሩ የኮንትራት ውል ስምምነት የፊርማ ስነ ስርዓት ከተካሄደባቸው ሁለት ትላልቅ ግንባታዎች መካከል፣ የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ግንባታ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ ርክክብ መርሃ ግብር፣ ዛሬ መስከረም 27 ቀን 2015 ዓ.ም የሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽ/ቤት ከፍተኛ አመራርና ባለሙያዎች፣ የሆስፒታሉ አመራሮች፣ የሲጎር አማካሪ ድርጅትና የዮሃንስ ሃይሌ ኮንስትራክሽን ድርጅት ተወካዮች በተገኙበት፣ የግንባታ ቦታ ምልከታና የስራ ማስጀመሪያ ርክክብ ስነ ስርዓት ተካሄዷል፡፡
በተካሄደው የግንባታ ስራ ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽ/ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ደቦ ቱንካ (ኢንጅነር) ባስተላለፉት የስራ መመሪያ፣ በዛሬው እለት የፕሮጀክት ግንባታው እንዲጀመር የተደረገበትና ትልቅ ትርጉምም የሚያሰጠው፤ የሰዎች የጤና አገልግሎት የማግኘት ጉዳይ ስለሆነ፤ የታማሚዎችን እንግልት የሚቀርፍ ሰው ተኮር ፕሮጀክት አንደመሆኑ፤ የተያዘለት የ18 ወራት የግንባታ ጊዜ ቆይታን አጭር በሚያደርግ ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ፣ ልዩ ትኩረት የሚስፈልገው ስራ ነው በማለት አጽንኦት ሰጥተዋል፡
አክለውም ዮሃንስ ሃይሌ ኮንስትራክሽን፣ ስራውን በሚያከናወንበት ሂደት ውስጥ፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ተሻግሮ መሄድ የሚያስችል አቅም ፈጥሮ፤ በገባው ቃል መሰረት፣ ገንብቶ ማስረከብ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ብርሃኑ አበራ በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ በመጀመሩ የሆስፒታሉን አመራርና ባለሙያዎች እጅግ በጣም ያስደሰተ ተግባር መሆኑን በመግለጽ፤ ለዚህም ትልቁ ምክንያት ሰዎች ለህክምና መጥተው መርዳት ሲገባን ባለን የህክምና ቦታ እጥረት፣ በርካቶች ሲንገላቱ እና ባስ ሲልም ህይወታቸው ሲያልፍ ማየት ከባድ እንደመሆኑ፤ ይህንን መሰል ችግር በመቅረፍና የጤናውን አገልግሎት ዘርፍ ማስፋትና ማዘመን የሚያስችል ስራ በመሆኑ፤ ፕሮጀክቱ ባጠረ ጊዜ እንዲጠናቀቅ የሆስፒታሉ አመራርና አጠቃላዩ ሰራተኛ ተገቢውን ትብብር ሁሉ ያደርጋል ብለዋል ፡፡
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ለተኝቶ ታካሚ 200 አልጋዎች፣26 የምርመራ ክፍሎች፣ ፋርማሲ (ከትልቅ የመድሃኒት ማከማቻ ጋር) ፣ ለህፃናትና አዋቂዎች አይ. ሲ. ዩ. ማዕከልና ሌሎች በርካታ የህክምና አገልግሎት መስጫ ማእከላትና መሰረተ ልማትን በውስጡ የሚይዝ የግንባታ ፕሮጀክት ይሆናል፡፡