በሃገር ህልውና እና ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል በወጣ አዋጅ ቁጥር 5/2014 አንቀፅ 10/1/ መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ መመሪያ አውጥቷል፡፡
መመሪያ ቁጥር 2 /2014
በሀገራችን ዘመናዊ የመታወቂያ አሰጣጥ ስርዓት ያልተዘረጋ በመሆኑ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት መደበኛውን የመታወቂያ አሰጣጥ ስርዓትን ለማስቀጠል አስቸጋሪ በመሆኑ መደበኛውን የመታወቂያ አሰጣጥ ስርዓት ለጊዜው በማገድ ጊዜያዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወቂያ አሰጣጥ ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣
በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍል የሚገኙ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ዜጎች በመደበኛው የመታወቂያ አሰጣጥ ሂደት መታወቂያ ያላገኙ በመሆኑ ለነዚህ ዜጎች ጊዜያዊ መታወቂያ በመስጠት ሰላማዊውን ህብረተሰብ ከፀረ-ሰላም ቡድኖች ለመለየት የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሆኖ በመገኘቱ፣
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንቀፅ 6(6) ላይ ለመታወቂያነት የሚያገለግሉ ሰነዶች የሌለው ሰው ይህን ጉዳይ በተመለከተ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙ ዝርዝር የአፈፃጸም መመሪያ ባወጣ በሁለት ሳምንት ውስጥ በአቅራቢያው በሚገኝ የቀበሌ፣ የወረዳ የፀጥታ እና አስተዳደር ፅህፈት ቤት ወይም ፖሊስ ጣቢያ በመመዝገብ ጊዜያዊ የመታወቂያ ወረቀት የመያዝ ግዴታ እንዳለበት የተደነገገ በመሆኑና ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የሕግ ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ፣
በሃገርን ህልውና እና ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል በወጣ አዋጅ ቁጥር 5/2014 አንቀፅ 10/1/ መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ይህን መመሪያ አውጥቷል፡፡
ክፍል አንድ
ጠቅላላ ድንጋጌዎች
1. አጭር ርዕስ
ይህ መመሪያ “የጊዜያዊ መታወቂያ አሰጣጥ ስርዓት መመሪያ ቁጥር 2/2014″ ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፣
2. ትርጓሜ
በዚህ መመሪያ ውስጥ፡-
1) አዋጅ ማለት በሃገር ህልውና እና ሉዐላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5/2014 ነው፣
2) ጊዜያዊ መታወቂያ ማለት በዚህ መመሪያ መሰረት የሚሰጥ መታወቂያ ነው፣
3) ክልል ማለት በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 47 መሰረት የተቋቋመ ክልል ሲሆን ለዚህ መመሪያ ዓላማ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ያካትታል፤
4) በአዋጁ ትርጉም የተሰጣቸው ቃለትና ሀረጎች ለዚህ መመሪያም ተፈፃሚነት አላቸው፡፡
3. የተፈፃሚነት ወሰን
ይህ መመሪያ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጸንቶ በሚቆይበት ጊዜ ሁሉ በየትኛውም የኢትዮጵያ ከተማ ላይ ተፈፃሚነት ይኖረዋል፡፡
ክፍል ሁለት
ጊዜያዊ መታወቂያ እንዲወስዱ የማይገደዱ ሰዎች እና ስለ ጊዜያዊ መታወቂያ አሰጣጥ ስርዓት
4. ጠቅላላ
1) የነዋሪነት መታወቂያ፣ የመንጃ ፈቃድ፣ ፓስፖርት ወይም ከነዚህ ተመጣጣኝ የሆነ መታወቂያ ሰነድ ያለው ሰው ጊዜያዊ መታወቂያ እንዲያወጣ አይገደድም፡፡
2) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ፀንቶ በሚቆይበት ወቅት መደበኛ መታወቂያ ማውጣትን አስመልክቶ የሚጣሉ ገደቦች፣ ከልከላዎች ወይም የሚተላለፉ ትዕዛዞች የመታወቂያ እድሳት ላይም ተፈፃሚ ይሆናሉ።
5. ተመጣጣኝ መታወቂያ ሰነዶች
የሚከተሉትን ሁኔታዎች ያሟሉ ሰዎች ተመጣጣኝ የሆነ መታወቂያ ሰነድ እንዳላቸው ተቆጥረው ጊዜያዊ መታወቂያ እንዲወሰዱ አይገደዱም፡
1) በሚሰሩበት ተቋም ወይም ድርጅት የተሰጠ የሰራተኛነት መታወቂያ ያላቸው የመንግስት ሰራተኞች፣ ሕጋዊ ሰውነት ያለው የንግድ ድርጅት ሰራተኞች፣የመንግስት የልማት ድርጅት ሰራተኞች፣ ህጋዊ ሰውነት ያለው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሰራተኞች፣
2) አግባብነት ካለው አካል የተሰጣቸው የማንነት መታወቂያ ያላቸው ስደተኞች፣
3) ህጋዊ እውቅና ካለው የትምህርት ተቋም የተማሪነት መታወቂያ ያላቸው ተማሪዎች፡፡
6. ስለ መስፈርቶች
ማንኛውም እድሜው 18 ዓመት የሞላው ሰው የሚከተሉትን መስፈርቶች ካሟላ ጊዜያዊ መታወቂያ እንዲሰጠው ማመልከት ይችላል፡-
1. የአዲስ አበባ ነዋሪ ስለመሆኑ ህጋዊ የመኖሪያ መታወቂያ ያለው እና በአካባቢው ነዋሪነት የሚታወቅ የቤተሰብ ሃላፊ ስለአመልካቹ ማንነት እና ሰላማዊነት ሙሉ ሃላፊነቱን በመውሰድ ዋስ ሆኖ ለጊዜያዊ መታወቂያ የቀረበውን ማመልከቻ ከደገፈ፣ ወይም
2. አሁን ከሚኖርበት አካባቢ ውጪ ሌላ ቦታ ሲኖር የነበረ ሆኖ ከነበረበት ቦታ ሸኚ ወረቀት ማምጣት የሚችልና አሁን የሚኖርበት ቤት ህጋዊ ሰነድ ያለው ሆኖ የቤቱ ባለቤት ወይም ህጋዊ ወኪሉ ካስመዘገበው ወይም ዋስ ለመሆነ ፍቃደኛ ከሆነ፤
3. በካምፕ፣ በማሰልጠኛ ወይም በአባላት የጋራ መኖሪያ ቤት የሚኖሩ የፖሊስ ሰራዊት ወይም የመከላከያ ሰራዊት አባላት ቤተሰባቸውና ራሳቸው በሚኖሩበት ቤት ቁጥር አገልግሎቱን እንዲያገኙ ከሚመለከተው አካል ተፈቅዶ ደብዳቤ ከተፃፈላቸው፣
4. ጊዜያዊ መታወቂያ እንዲሰጥ ጥያቄ በቀረበበት አካባቢ ነዋሪ የሆነ ባለትዳር ባል ወይም ሚስት ከሌላ ቦታ በስራ ምክንያት የተዛወረ ከሆነና ስለመዘዋወሩ እና ህጋዊ ትዳር ስለመኖሩ በቂ ማስረጃ ካቀረበ፣
7. የጊዜያዊ መታወቂያ የጊዜ ቆይታ እና ስለሚይዛቸው መረጃዎች
1. ጊዜያዊ መታወቂያ የሚሰጠው ለ6 ወር ሲሆን መታወቂያውን የያዘው ሰው በየወሩ መታወቂያውን የወሰደበት ቦታ በመቅረብ ሪፖርት ማድረግና ማሳደስ ይኖርበታል፣
2. ጊዜያዊ መታወቂያ ላይ ግለሰቡ በአስራ አምስት ቀናት ውስጥ የተነሳው ፎቶ የሚለጠፍ ሆኖ በመታወቂያው ላይ የሚሰፍሩ መረጃዎች ይዘት መደበኛው መታወቂያ የሚይዛቸው መረጃዎች ይሆናሉ::
8. ጊዜያዊ መታወቂያ የመስጠት ሀላፊነት ያለባቸው አካላት
የሚከተሉት አካላት ጊዜያዊ መታወቂያ የመስጠት ሀላፊነት አለባቸው፡-
1) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፅጥታ መዋቅር፣
2) በድሬዳዋ እና በክልሎች ደግሞ የፖሊስ መዋቅር፡፡
9. ማንነትን ስለማረጋገጥ
ጊዜያዊ መታወቂያ ለመውሰድ የሚያመለክት ማንኛውም ግለሰብ ስለትክክለኛ ማንነቱ መታወቂያውን በሚወስድበት ቦታ በመንግስት አካል በሚዘጋጅ ቅፅ ላይ የተመለከቱ ማንነትን ለማረጋገጥ የሚጠቅሙ መረጃዎችን በመሙላትና ቃለ መሀላ በመፈጸም ያረጋግጣል።
10. የጊዜያዊ መታወቂያ አገልግሎት
በዚህ መመሪያ መሰረት የሚሰጥ ጊዜያዊ መታወቂያ መታወቂያውን የወሰደውን ሰው ማንነትን ከማረጋገጥ ውጪ መደበኛው የነዋሪነት መታወቂያ የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ወይም መብቶች አያስገኝም፡፡
ክፍል ሶስት
ግዴታዎችና የተከለከለ ተግባራት
11. ማህበራዊ ጉዳይን የሚመለከት ተግባርና ሀላፊነት ያለባቸው የመንግስት ተቋማት ግዴታዎች
ማህበራዊ ጉዳይን በተመለከተ ሀላፊነት ያለባቸው የፌዴራልና የክልል የመንግስት ተቋማት ከሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በተባበር ጎዳና ተዳዳሪዎችን፣ ቋሚ አድራሻ እና ስራ የሌላቸውንና ሌሎች በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በማደራጀት ወደ መጠለያ ወይም ጊዜያዊ መቆያ እንዲገቡ እና በዚያ ቦታ እንዲቆዩ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡
12. ጊዜያዊ መታወቂያ የወሰደ ሰው እና የመታወቂያ ሰጪው አካል ግዴታዎች
1) ጊዜያዊ መታወቂያ የጠፋበት፣ የተበላሸበት ወይም በሌላ ምክንያት ጉዳት የደረሰበት ወይም በማናቸውም ምክንያት ከእጁ የወጣበት ማንኛውም ሰው ለፖሊስ በ24 ሰዓት ውስጥ ሪፖርት የማድረግ ሀላፊነት አለበት፣
2) በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 1 የተመለከተው ሁኔታ ሪፖርት ፖሊስ ተቋም በሚሰጠው ማረጋገጫ መሰረት ጊዜያዊ መታወቂያ የመስጠት ስልጣን የተሰጠው አካል፣ ምትክ ጊዜያዊ መታወቂያ ይሰጣል::
13. የተከለከሉ ተግባራት
የሚከተሉትን ተግባራት መፈጸም በአዋጁ እና ሌሎች ህጎች መሰረት የወንጀል ኃላፊነት ያስከትላል፡-
1) ጊዜያዊ መታወቂያ ለመውሰድ ሀሰተኛ መረጃ መስጠት ፣
2) መስፈርቱን ለማያሟላ ሰው ጊዜያዊ መታወቂያ መስጠት፤
3) መስፈርቱን የማያሟላ ሰው ጊዘያዊ መታወቂያ እንዲሰጠው በማሰብ ማረጋገጫ ደብዳቤ መፃፍ ወይም ምስክር መሆን፣
4) ከአንድ በላይ ጊዜያዊ መታወቂያ ይዞ መገኘት፡፡
ክፍል አራት
ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች
14. ተፈፃሚነት የሌላቸው መመሪያዎች ወይም ልማዳዊ አሰራሮች
ከዚህ መመሪያ ጋር የሚቃረን ማንኛዉም መመሪያ ወይም የአሰራር ልምድ በዚህ መመሪያ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ይህ መመረያ ጸንቶ በሚቆይበት ጊዜ ተፈፃሚነት አይኖረዉም፡፡
15. መመሪያዉ የሚፀናበት ግዜ
ይህ መመሪያ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡
አዲስ አበባ ጥቅምት 6 ቀን 2014 ዓ.ም
የአስቸካይ ጊዜ አዋጅ መመሪያ እዝ