የአዲሰ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ እንዲሁም ተጠሪ ተቋማት ከጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ ጋር በመተባበር በቦሌ ቡልቡላ ማሪያም ማዞሪያ የጋራ መኖሪያ ቤት በመገኘት ከ75 ሺህ በላይ ለምግብነት እና ለአካባቢ ውበት የሚያገለግሉ ችግኞች ተከላ መርሐግብር ተጀምሯል ።
በችግኝ ተከላ መርሐግብር የአዲሰ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መስከረም ዘውዴ እንደገለፁት በከተማዋ የተለያዩ የጋራ መኖሪያ ቤት ሳይቶች ነዋሪዎች በማህበር በመደራጀት የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ቅጥር ጊቢን የማስዋብ ስራ በማከናወን ላይ ይገኛሉ ።
ይህን የማስዋብ እና አረንጓዴ በማልበስ ምቹ የመኖሪያ አካባቢን እንዲሆን ነዋሪዎች እያደረጉት ያለውን ተሳትፎ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ኃላፊዋ ተናግረዋል ።
በቢሮው ስር ባሉ ከ18 በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችም የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐግብርን ለማከናወን ከ75ሺህ በላይ ለምግብነት እና ለአካባቢ ውበት የሚያገለግሉ ችግኞች መዘጋጀቱን ዶ/ር መስከረም ገልጸዋል ።
የጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አልማው ጋሪ በበኩላቸው በቀጣይም ከከተማ አሰተዳደሩ እና ከቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ በመቀናጀት ከቤት ልማቱ ባሻገር በተለያዩ የማህበራዊ እና የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ እንደሚሳተፉ ገልጸዋል፡፡