የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይል በአዲስ አበባ ዋና ዋና መንገዶች ላይ ያደረገውን የአጀብና የፀጥታ ሥራዎች የተግባር ልምምድ በስኬት ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡
ዛሬ የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይል ከቀናት በኋላ በመዲናዋ በሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለሚከናወኑ የአጀብ እና የፀጥታ ስራዎችን ሁሉም የፀጥታ አካላት የተሳተፉበት ወታደራዊ የተግባር ልምምዱን በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ላይ በስኬት አከናውኗል ተብሏል፡፡
በተለያዩ ጊዚያት የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይሉ ታላላቅ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ጉባዔዎችን በሰላም እንዲጠናቀቁ ሥራውን የሚመጥን ተግባራዊ ልምምድ ሲያደርግ መቆየቱን የሚታወስ ሲሆን÷ መጪውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን ምክንያት በማድረግም የአጀብ እና የፀጥታ ስራዎችን መሰረት ያደረገ ልምምድ አድርጎ አጠናቋል ነው የተባለው፡፡
በዚህም መላው የከተማዋ ነዋሪዎች ወታደራዊ ልምምዱ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ላሳዩት ቀና ተባባሪነት የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይሉ ምስጋና አቅርቧል፡፡
ለመጪው ለአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤም የከተማዋ ነዋሪዎች የተለመደውን ትብብር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪውን አቅርቧል፡፡