የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአሜሪካ ቆይታ ኢትዮጵያ ያላትን የዲፕሎማሲ አቅም ከፍ ያደረገ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመገናኛ ብዙሀን መግለጫ ሰጥተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ በመግለጫቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይና የሉዑካን ቡድናቸው በአሜሪካ የተሳካ ቆይታ አድርገው ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ አፍሪካ ጉባኤ ተገኝተው ከጉባኤው ጎን ለጎን ከአሜሪካ መሪዎችና ጋር ውጤታማ ውይይቶችን ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በውይይቱ የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ሰላምን ለማምጣት የወሰደው እርምጃ እውቅና ያገኘበት መሆኑንም አመላክተዋል።
በተለይ ለስምምነቱ ትግበራ ያሳየው ቁርጠኝነት አድናቆት እንደተቸረው እንዲሁ።
አሜሪካና ኢትዮጵያ በጋራ የሚሰሯቸውን የልማትና ሌሎች በርካታ ጉዳዮችን አጠናክረው ለማስቀጠል መስማማታቸውንና ሁለትዮሽ ግንኙነቱን ወደ ቀደመ መልኩ ለመመለስ እንደሚሰራም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ሚሊየኖችን አስተባብራ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን መትከል መቻሏና ወደ ሌሎች አፍሪካ ሀገራት ለማስፋት የምታደርገው ጥረት እውቅና የተሰጠበት መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለዋል።
በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ለመልሶ ግንባታ የምታደርገውን ጥረት አለም አቀፍ ድጋፎች የተገኘበት እንዲሁም ለቀጣይ ድጋፎችም መሰረት የተጣለበት ቆይታ መሆኑንም አመላክተዋል።
በአጠቃላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሜሪካ ቆይታ በዲፕሎማሲ መስክ ስኬት የተመዘገበበት እና ኢትዮጵያ ያላትን የዲፕሎማሲ አቅም ከፍ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።