የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት አካሄደ።
የውይይቱ ዓላማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት አባቶች ከፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ጋር በመተባበርና በመናበብ በዓሉን ሰላማዊ እንዲሆን ለማስቻል መሆኑም ነው የተገለጸው።
በመድረኩም የከተራና የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፥ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ ከዚህ በፊት ሃይማኖታዊና የህዝብ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ውጤታማ ስራ ማከናወኑን ገልጸዋል።
የዘንድሮ የከተራና የጥምቀት በዓላት በአገር አቀፍ ደረጃ በሰላም እንዲከበሩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።
የጋራ ግብረ-ኃይሉ በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር ለማድረግ በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች በርካታ የፀጥታ አካላት ማሰማራቱን ገልጸው፤ በታቦታት ማደሪያ ስፍራዎችና በርካታ የበዓሉ ታዳሚዎች በሚገኙበት አካባቢ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
የሀገራችንን ሰላም ለማደናቀፍ የሚፈልጉ የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችን ህዝብ የሚሰበሰብበትን አጋጣሚ ተጠቅመው ሰላም ሊያውኩ ስለሚችሉ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱንም ነው የተናገሩት።
በዚህ ረገድ ፖሊስ ቀደም ብሎ ባደረገው ፍተሻና አሰሳ በርካታ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ነው ያነሱት።
ፖሊስ ሁሌም ከህዝብ ጋር ተቀራርቦ ይሰራል ያሉት ከሚሽነር ጄነራሉ፤ የዘንድሮ የከተራና የጥምቀት በዓላት በሰላም እንዲከበሩም ከሃይማኖት አባቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ቀደም ብሎ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።
የውይይት መድረኩም የዚሁ ስራ አካል ስለመሆኑ ነው ያነሱት።
በመሆኑም የሃይማኖት አባቶች የአብሮነትና የሰላም መገለጫ የሆነውን በዓል ለፖለቲካ ትርፋቸው ለማዋል የሚሰሩ አካላትን በመከላከል ረገድ ከጸጥታ ተቋማት ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት አባቶች በበኩላቸው፥ በዓሉ በሰላም እንዲከበር ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተው የጋራ አቋም መያዛቸውን ገልፀዋል።
ጥምቀት ሃይማኖታዊና የሰላም በዓል መሆኑን የተናገሩት አባቶቹ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች በዓሉ በሰላም እንዲከበር ኃላፊነት ወስደው የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የጥምቀት በዓል ከኢትዮጵያ ባለፈ የዓለም ቅርስ መሆኑን በማንሳት፤ የክብረ በዓሉ ተሳታፊዎች ይህን በሚመጥን መልኩ በሰላም እንዲከበር ሚናቸውን በመወጣት የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ ለዓለም ማስተዋወቅ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
በዓሉ በሰላም ተከብብሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ የጸጥታ ኃይሎችና የሚለከተቻው ባለድርሻ አካላት ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸውም ነው የሃይማኖት አባቶቹ የጠየቁት።
የበዓሉ በሰላም መከበር የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ቤተክርስቲያኗ ይህን ታሳቢ በማድረግ ለወጣቶች ስልጠና መስጠቷን ተናግረዋል።
የሃይማኖት አባቶች ህግና ስርዓትን በማክበር እንዲሁም ለሰላም መከበር አርአያ በመሆን ሃይማኖታዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ነው የጠየቁት።
የጥምቀት በዓል በዓለም አቀፍ ደረጃ በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበ በዓል ሲሆን፤ ኢትዮጵያውያን በነፃነት በአደባባይ ወጥተው በጋራ የሚያከብሩት፣ የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን የበለጠ የሚያጠናክሩበት፣ መንፈሳዊ እሴቶቻቸውን የሚያዳብሩበትና በጋራ መኖርን ለመላው ዓለም በምሳሌነት የሚያሳዩበት በዓል ነው።