በአንድ ጀንበር ከ1 ሚሊዮን በላይ የችግኝ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የተፋሰስና አረንጓዴ አካባቢዎች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ጺዮን ተሾመ እንደገለጹት “ኑ አዲስ አበባን እናልብስ” በሚል ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐግብር በተለያዩ ስፍራዎች እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የዚሁ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐግብር አካል የሆነው በአንድ ጀንበር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ችግኝ የመትከል መርሐግብር የፊታችን እሁድ ሀምሌ 4 ቀን 2013 ዓ.ም በመላው አዲስ አበባ እንደሚካሄድ ኢ/ር ጺዮን ተናግረዋል፡፡
ለመርሐግብሩ የሚሆን የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች ቁፋሮን ጨምሮ ሀገር በቀል እና ለምግብነት እንዲሁም ለአካባቢ ውበት የሚጠቅሙ ችግኞች ከወዲሁ ዝግጁ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በችግኝ ተከላ መርሐግብሩ የፌደራል እና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣የስፖርት ቤተሰቦች፣የሀይማኖት አባቶች ፣የጽጥታ አካላት ፣ወጣቶች እና ልዩ ልዩ ህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ዋና ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል፡፡