የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የነዋሪው አንገብጋቢ ጥያቄ የሆነውን የቤት አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ በመንግስት እና የግል አጋርነት ( Public-Private Partnership) በ70/30 መርህ 100ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ዛሬ ከአልሚዎች ጋር ተፈራርሟል::
መካከለኛ ገቢ ያላቸው የከተማችን ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የዚህ የ100ሺህ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ የሚጀመር ይሆናል::
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የረዥም ዘመን የነዋሪዎች ጥያቄ የሆነው የቤት አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ ጥያቄው በመንግስት ብቻ የሚመለስ ባለመሆኑ ልበ ቀና ባለሃብቶችን በማሳተፍ እና አዳዲስ አሰራሮችን በመተግበር ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል::
በመንግስት እና የግል አጋርነት ለሚገነባው የቤት ግንባታ ፕሮጀክት የከተማ አስተዳደሩ በቂ መሬት እንዳዘጋጀ የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ግንባታውን በአጭር ግዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እና የህዝባችንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የከተማ አስተዳደሩ የግንባታ ሂደቱን በቅርበት እንደሚከታተል ገልፀዋል::